Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 25 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ለመገናኛው ድንኳን የሚቀርቡ ስጦታዎች
25፥1-7 ተጓ ምብ – ዘፀ 35፥4-9

1 እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤

2 “ስጦታ እንዲያመጡልኝ ለእስራኤላውያን ንገራቸው። ይሰጥ ዘንድ ልቡ ካነሣሣው ከእያንዳንዱ ሰው ስጦታን ተቀበልልኝ።

3 “ከእነርሱ የምትቀበላቸው ስጦታዎች እነዚህ ናቸው፤ “ወርቅ፣ ብርና፣ ንሓስ፤

4 ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና የበፍታ ድር ልብስ፣ የፍየል ጠጕር፤

5 ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቈዳ፣ የለፋ ቈዳ፣ የግራር ዕንጨት፤

6 ለመብራት የወይራ ዘይት፤ ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ መዐዛ ላለው ዕጣን የሚሆኑ ቅመሞች፤

7 በኤፉድና በደረት ኪስ ላይ የሚሆኑ መረግዶችና ሌሎች ዕንቍዎች።

8 “ከዚያም መቅደስ እንዲሠሩልኝ አድርግ፤ እኔም በመካከላቸው ዐድራለሁ።

9 ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ ያለውን ዕቃ ሁሉ ልክ እኔ በማሳይህ ዕቅድ መሠረት ሥሩት።


የቃል ኪዳኑ ታቦት
25፥10-20 ተጓ ምብ – ዘፀ 37፥1-9

10 “ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት ከግራር ዕንጨት እንዲሠሩ አድርግ።

11 ውስጡንም ውጭውንም በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አብጅለት።

12 አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ ሁለቱን በአንድ በኩል ሁለቱን በሌላ በኩል ከአራቱ እግሮች ጋራ አያይዝ።

13 ከዚያም መሎጊያዎችን ከግራር ዕንጨት ሥራ፤ በወርቅም ለብጣቸው።

14 መሎጊያዎችንም መሸከሚያ እንዲሆኑ በታቦቱ ማእዘኖች ላይ ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው።

15 መሎጊያዎቹ ከታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ምን ጊዜም መውጣት የለባቸውም።

16 የምሰጥህንም ምስክር በታቦቱ ውስጥ አኑር።

17 “ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ከንጹሕ ወርቅ ሥራለት።

18 በስርየት መክደኛው ዳርና ዳር ላይ የሚሆኑ ከወርቅ የተቀረጹ ሁለት ኪሩቤል ሥራ።

19 አንዱን ኪሩብ በአንደኛው፣ ሁለተኛውን ኪሩብ በሌላኛው ዳር አድርግ በሁለቱም ጫፎች ሁለቱን ኪሩቤል ከስርየት መክደኛው ጋራ አንድ ወጥ አድርገህ ሥራቸው።

20 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት የስርየት መክደኛውን በክንፎቻቸው ይሸፍኑ፤ እርስ በርሳቸው ትይዩ በመሆንም ፊታቸውን ወደ ስርየት መክደኛው ያድርጉ።

21 የስርየት መክደኛውን በታቦቱ ዐናት ላይ አስቀምጠው፤ እኔ የምሰጥህን ምስክሩንም በታቦቱ ውስጥ አስቀምጥ።

22 በምስክሩ ታቦት ላይ ባሉት በሁለቱ ኪሩቤል መካከል፣ በስርየት መክደኛው ላይ በዚያ እኔ ከአንተ ጋራ እገናኛለሁ፤ ለእስራኤላውያን የሚሆኑትን ትእዛዞቼንም እሰጥሃለሁ።


የኅብስቱ ማስቀመጫ ጠረጴዛ
25፥23-29 ተጓ ምብ – ዘፀ 37፥10-16

23 “ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ጠረጴዛ ከግራር ዕንጨት ሥራ።

24 በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አድርግለት።

25 ዙሪያውንም አንድ ስንዝር ስፋት ያለው ጠርዝ አብጅለት፤ በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ አድርግለት።

26 ለጠረጴዛው አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ፣ አራቱ እግሮች ባሉበት በአራቱ ማእዘኖች ላይ አያይዘው።

27 ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች ይይዙ ዘንድ፣ ቀለበቶቹ ከክፈፉ አጠገብ ይሁኑ።

28 መሎጊያዎቹን ከግራር ዕንጨት ሥራቸው፤ በወርቅ ለብጣቸው፤ ጠረጴዛውንም ተሸከምባቸው።

29 ለመጠጥ ቍርባን መፍሰሻ ይሆኑም ዘንድ ዝርግ ሳሕኖችንና ወጭቶችን፣ እንዲሁም ማንቈርቈሪያዎቹንና ጐድጓዳ ሳሕኖቹን ከንጹሕ ወርቅ ሥራቸው።

30 በማንኛውም ጊዜ በፊቴ እንዲሆን በገጸ ኅብስቱ በዚህ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጥ።


የመብራቱ መቅረዝ
25፥31-39 ተጓ ምብ – ዘፀ 37፥17-24

31 “ከንጹሕ ወርቅ መቅረዝ ሥራ፤ መቆሚያና ዘንግ አብጅለት፤ ጽዋ መሰል አበባዎች፣ እንቡጦችና የፈነዱ አበባዎች ከመቅረዙ ጋራ ወጥ ሆነው ይሠሩ።

32 ከመቅረዙ ግራና ቀኝ ጐን ጋራ የተያያዙ፣ በአንዱ በኩል ሦስት በሌላው በኩል ሦስት በድምሩ ስድስት ቅርንጫፎች ይኑሩት።

33 ከመቅረዙ ጋራ የተያያዙት ስድስቱ ቅርንጫፎች እያንዳንዳቸው እንቡጥና ቀንበጥ ያሏቸው የለውዝ አበባ ቅርጽ ያሏቸው ሦስት ጽዋ መሰል አበባዎች ጋራ ያኑሯቸው።

34 በመቅረዙም ላይ አበባዎች እንቡጥና ቀንበጥ ያሏቸው አራት የለውዝ አበባ ቅርጽ ያሏቸው ጽዋዎች ይኑሩ።

35 በመቅረዙ ላይ ላሉት ለስድስቱ ቅርንጫፎች እንቡጥ በመጀመሪያዎቹ ጥንድ ቅርንጫፎች ሥር፣ ሁለተኛውም እንቡጥ በሁለተኛው ጥንድ ሥር፣ ሦስተኛውም እንቡጥ በሦስተኛው ጥንድ ሥር ይሁን።

36 እንቡጦቹና ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከመቅረዙ ጋራ አንድ ወጥ ሆነው ከንጹሕ ወርቅ ተቀርጸው ይሠሩ።

37 “ከዚያም ሰባት መብራቶች ሠርተህ ከመቅረዙ ፊት ለፊት ለሚገኘው ስፍራ ብርሃን እንዲሰጡ ከመቅረዙ ላይ አስቀምጣቸው።

38 መኰስተሪያና የኵስታሪ ማስቀመጫ ሳሕኖቹም ከንጹሕ ወርቅ ይሠሩ።

39 ለመቅረዙና ለዕቃዎቹ ሁሉ የሚያስፈልገው አንድ መክሊት ንጹሕ ወርቅ ነው።

40 በተራራው ላይ በተገለጠልህ ምሳሌ መሠረት መሥራትህን ልብ በል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告