Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 23 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የፍትሕና የምሕረት ሕጎች

1 “የሐሰት ወሬ አትንዛ፤ ተንኰል ያለበትን ምስክርነት በመስጠት ክፉውን ሰው አታግዝ።

2 “ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል፤ በሕግ ፊት ምስክርነት ስትሰጥ፣ ከብዙዎቹ ጋራ ተባብረህ ፍትሕ አታጣምም።

3 በዳኝነት ጊዜ ለድኻው አታድላ።

4 “የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ሲባዝን ብታገኘው ወደ እርሱ መልሰው።

5 የሚጠላህ ሰው አህያ፣ ጭነት ከብዶት ወድቆ ብታየው ርዳው እንጂ ትተኸው አትሂድ።

6 “በዳኝነት ጊዜ በድኻው ላይ ፍርድ አታጓድልበት።

7 ከሐሰት ክስ ራቅ፤ በደል የሌለበትን ወይም ጻድቁን ሰው ለሞት አሳልፈህ አትስጥ፣ በደለኛውን ንጹሕ አላደርግምና።

8 “ጕቦ አትቀበል፤ ጕቦ አጥርተው የሚያዩትን ሰዎች ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና።

9 “መጻተኛውን አትጨቍን፤ በግብጽ መጻተኛ ስለ ነበራችሁ፣ መጻተኛ ምን እንደሚሰማው እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና።


የሰንበት ሕጎች

10 “ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ አዝመራንም ሰብስብ፤

11 ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱን ሳትጠቀምባትና ሳታርሳት እንዲሁ ተዋት፤ ከዚያም በወገንህ መካከል ያሉት ድኾች ከርሷ ምግብ ያገኛሉ፤ የዱር አራዊትም ከእነርሱ የተረፈውን ይበላሉ። በወይን ቦታህና በወይራ ዛፎችህም ላይ እንዲሁ አድርግ።

12 “ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ በቤትህ የተወለደው ባሪያና መጻተኛው ያርፉ ዘንድ በሰባተኛው ቀን ምንም አትሥራ።

13 “ያልኋችሁን ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ተጠንቀቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፤ ከአፋችሁም አይስሙ።


ሦስቱ ዐውደ ዓመታዊ በዓላት

14 “በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓልን ታከብራላችሁ።

15 “የቂጣ በዓልን አክብር፤ እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን እርሾ የሌለውን ቂጣ ብላ፤ ይህንም በአቢብ ወር በተወሰነ ቀን አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብጽ ወጥተሃልና። “ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ።

16 “በማሳህ ላይ በዘራኸው እህል በኵራት የመከርን በዓል አክብር። “በዓመቱ መጨረሻ በማሳህ ላይ ያለውን እህልህን ስትሰበስብ የመክተቻውን በዓል አክብር።

17 “በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይቅረብ።

18 “የመሥዋዕትን ደም እርሾ ካለበት ነገር ጋራ አድርገህ ለእኔ አታቅርብ። “የበዓል መሥዋዕቴ ስብ እስከ ንጋት ድረስ አይቈይ።

19 “የምድርህን ምርጥ ፍሬ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቤት አምጣ። “ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።


የእግዚአብሔር መልአክ መንገድ ስለ መምራቱ

20 “እነሆ፤ በጕዞ ላይ ሳለህ የሚጠብቅህንና ወዳዘጋጀሁልህ ስፍራ የሚያስገባህን መልአክ በፊትህ ልኬልሃለሁ።

21 በጥንቃቄ ተከተለው፤ የሚናገረውንም ልብ ብለህ ስማው፤ አታምፅበት። ስሜ በርሱ ላይ ነውና ዐመፅህን ይቅር አይልም።

22 የሚናገረውን በጥንቃቄ ብታደምጥና ያልኩህን ሁሉ ብታደርግ ለጠላቶችህ ጠላት እሆናለሁ፤ የሚቃወሙህን እቃወማለሁ።

23 መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ አንተንም ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ያስገባሃል፤ እኔም እነርሱን አጠፋቸዋለሁ።

24 ለአማልክታቸው አትስገድ፤ ወይም አታምልካቸው፤ ወይም ልምዳቸውን አትከተል፤ እነርሱን ማፈራረስ አለብህ፤ የአምልኮ ድንጋዮቻቸውንም ሰባብር።

25 አምላክህን እግዚአብሔርን አምልክ፤ በረከቱም በምትበላውና በምትጠጣው ላይ ይሆናል፤ በሽታንም ከአንተ ዘንድ አርቃለሁ።

26 በምድርህም የሚያስወርዳት ወይም መካን ሴት አትኖርም፤ ረዥም ዕድሜም እሰጥሃለሁ።

27 “በሚያጋጥሙህ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስፈራቴን በፊትህ እልካለሁ፤ ግራም አጋባቸዋለሁ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲሸሹ አደርጋለሁ።

28 ኤዊያውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን ከመንገድህ ለማስወጣት ተርብን በፊትህ እሰድዳለሁ።

29 ነገር ግን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አላወጣቸውም፤ ምክንያቱም ምድሪቱ ባድማ ሆና የዱር አራዊት ይበዙባችኋል።

30 ቍጥርህ ጨምሮ ምድሪቱን ለመውረስ እስክትበቃ ድረስ ጥቂት በጥቂት ከፊታችሁ አባርራቸዋለሁ።

31 “ድንበርህን ከቀይ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፣ ከምድረ በዳው እስከ ወንዙ ድረስ አደርገዋለሁ፤ በምድሪቱም ላይ የሚኖሩትን ሰዎች አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም አሳድደህ ከፊትህ ታስወጣቸዋለህ።

32 ከእነርሱም ሆነ ከአማልክታቸው ጋራ ኪዳን አታድርግ።

33 በምድርህ ላይ እንዲኖሩ አትፍቀድላቸው፤ አለዚያ እኔን እንድትበድል ያደርጉሃል፤ አማልክታቸውን ማምለክ በርግጥ ወጥመድ ይሆንብሃልና።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告