Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሙሴ መወለድ

1 በዚያ ጊዜ ከሌዊ ነገድ የሆነ አንድ ሰው አንዲት ሌዋዊት ሴት አገባ።

2 እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሕፃኑ መልከ መልካም መሆኑን ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው።

3 ከዚያ በላይ ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ ግን የደንገል ቅርጫት ወስዳ፣ በዝፍትና በቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም በውስጡ አስተኝታ ቅርጫቱን አባይ ወንዝ ዳር ቄጠማ መካከል አስቀመጠችው።

4 የሕፃኑም እኅት የሚደርስበትን ነገር ለማወቅ ራቅ ብላ ቆማ ታይ ነበር።

5 በዚህ ጊዜ የፈርዖን ልጅ ልትታጠብ ወደ አባይ ወንዝ ወረደች፤ በምትታጠብበትም ጊዜ ደንገጥሮቿ በወንዙ ዳር ወዲያና ወዲህ ይሉ ነበር፤ በቄጠማውም መካከል የተቀመጠ ቅርጫት አይታ ከደንገጥሮቿ አንዷን እንድታመጣው ላከቻት።

6 ቅርጫቱን ስትከፍተው ሕፃኑን በውስጡ አየች፤ ያለቅስ ስለ ነበርም ዐዘነችለትና፣ “ከዕብራውያን ሕፃናት አንዱ መሆን አለበት” አለች።

7 የሕፃኑ እኅት ለፈርዖን ልጅ፣ “ሕፃኑን እያጠባች የምታሳድግልሽ ከዕብራውያን ሴቶች መካከል ሞግዚት ላምጣልሽን?” አለቻት።

8 የፈርዖንም ልጅ፣ “መልካም፣ ሂጂ” አለቻት። ልጅቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ይዛ መጣች።

9 የፈርዖንም ልጅ ሴቲቱን፣ “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ ደመወዝ እከፍልሻለሁ” አለቻት። ሴትዮዋም ሕፃኑን ወስዳ አሳደገችው።

10 ሕፃኑም ባደገ ጊዜ ወደ ፈርዖን ልጅ አመጣችው፤ ልጇም ሆነ፤ እርሷም፣ “ከውሃ አውጥቼዋለሁና” ስትል ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው።


ሙሴ ወደ ምድያም ምድር ሸሸ

11 ሙሴ ካደገ በኋላ አንድ ቀን ወገኖቹ ወደሚገኙበት ስፍራ ወጣ፤ በዚያም ተገድደው ከባድ ሥራ ሲሠሩ ተመለከተ፤ ዕብራዊ ወገኑንም አንድ ግብጻዊ ሲደበድበው አየ።

12 ሙሴም አካባቢውን ቃኝቶ ማንም አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ፣ ግብጻዊውን ገድሎ አሸዋ ውስጥ ደበቀው።

13 በማግስቱም በወጣ ጊዜ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ ጥፋተኛውንም፣ “የገዛ ወገንህን የምትመታው ለምንድን ነው?” አለው።

14 ሰውየውም፣ “አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ግብጻዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፣ “ለካስ ያደረግሁት ነገር ታውቋል!” በማለት ፈራ።

15 ፈርዖንም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ፤ ሙሴ ግን ከፈርዖን ሸሽቶ ወደ ምድያም ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ በአንድ የውሃ ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ።

16 የምድያም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ውሃው ጕድጓድ መጥተው የአባታቸውን በጎች ውሃ ለማጠጣት ገንዳውን ሞሉት።

17 እረኞችም መጥተው ሴቶቹን ሲያባርሯቸው ሙሴ ከተቀመጠበት ተነሥቶ ተከላከለላቸው፤ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው።

18 ሴቶቹም ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤል በተመለሱ ጊዜ፣ “ዛሬስ ያለወትሯችሁ እንዴት ፈጥናችሁ ተመለሳችሁ?” አላቸው።

19 እነርሱም፣ “አንድ ግብጻዊ ከእረኞች እጅ አዳነን፤ እንዲያውም ውሃ ቀድቶ በጎቻችንን አጠጣልን” አሉት።

20 አባታቸውም፣ ሴቶች ልጆቹን “የት አለ? ለምን ትታችሁት መጣችሁ? ጥሩትና ዐብሮን እንጀራ ይብላ” አላቸው።

21 ሙሴም ከሰውየው ጋራ ለመኖር ተስማማ፤ ራጉኤልም ልጁን ሲፓራን ዳረለት።

22 ሲፓራም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሙሴም፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ሲል የልጁን ስም ጌርሳም ብሎ ጠራው።

23 ከብዙ ዓመት በኋላ የግብጽ ንጉሥ ሞተ፤ እስራኤላውያንም በባርነት ከደረሰባቸው ግፍ የተነሣ ይጮኹ ነበር፤ ከባርነት ቀንበር ለመላቀቅ ያሰሙትም ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ደረሰ።

24 እግዚአብሔርም የጩኸታቸውን ሲቃ ሰማ፤ ከአብርሃም፣ ከይሥሐቅና ከያዕቆብ ጋራ የገባውንም ቃል ኪዳን ዐሰበ።

25 እግዚአብሔርም እስራኤላውያንን ተመለከተ፤ ስለ እነርሱም ገደደው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告