Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 19 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በሲና ተራራ ላይ

1 በሦስተኛው ወር እስራኤላውያን ከግብጽ ለቅቀው በወጡበት በዚያችው ዕለት ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ።

2 ከራፊዲም ከተነሡ በኋላ ወደ ሲና ምድረ በዳ ገቡ፤ እስራኤልም በዚያ በምድረ በዳው በተራራው ፊት ለፊት ሰፈሩ።

3 ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከተራራው ጠራውና እንዲህ አለው፤ “ለያዕቆብ ቤት የምትለው ለእስራኤልም ሕዝብ የምትናገረው ይህ ነው፤

4 ‘በግብጽ ላይ ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል።

5 አሁንም በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣

6 እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤’ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃሎች እነዚህ ናቸው።”

7 ስለዚህ ሙሴ ተመልሶ የሕዝቡን አለቆች አስጠራ፤ እንዲናገር እግዚአብሔር ያዘዘውን ቃሎች ሁሉ ነገራቸው።

8 ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ላይ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ፤ ስለዚህ ሙሴ እነርሱ ያሉትን መልሶ ወደ እግዚአብሔር ወሰደ።

9 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ከአንተ ጋራ ስናገር ሕዝቡ እንዲሰሙኝና እምነታቸውን ምን ጊዜም በአንተ ላይ እንዲጥሉ በከባድ ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ” ከዚያም ሙሴ ሕዝቡ ያሉትን ለእግዚአብሔር ነገረው።

10 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ሕዝቡ ሂድና ዛሬና ነገ ቀድሳቸው፤ ልብሳቸውን እንዲያጥቡ አድርግ፤

11 በሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ ምክንያቱም በዚያ ቀን በሕዝቡ ፊት እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳል።

12 በተራራው ዙሪያ ለሕዝቡ ወሰን አበጅተህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ወደ ተራራው እንዳትወጡ ወይም ግርጌውን እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ማንም ተራራውን ቢነካ በርግጥ ይሞታል።

13 በድንጋይ ይወገራል ወይም በቀስት ይወጋል፤ ምንም እጅ በርሱ ላይ አያርፍም፤ ሰውም ሆነ እንስሳ በሕይወት እንዲኖር አይተውም።’ ወደ ተራራው መውጣት የሚችሉት ከፍ ባለ ድምፅ መለከት በተነፋ ጊዜ ብቻ ነው።”

14 ሙሴ ከተራራው ወርዶ ወደ ሕዝቡ ከሄደ በኋላ ቀደሳቸው፤ ልብሳቸውንም ዐጠቡ።

15 ከዚያም ለሕዝቡ፣ “ለሦስተኛው ቀን ራሳችሁን አዘጋጁ፤ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከማድረግ ተቈጠቡ” አላቸው።

16 በሦስተኛውም ቀን ጧት ከባድ ደመና በተራራው ላይ ሆኖ ነጐድጓድና መብረቅ እንዲሁም ታላቅ የቀንደ መለከት ድምፅ ነበር፤ በሰፈሩ ያሉት ሁሉ ተንቀጠቀጡ።

17 ከዚያም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋራ ለማገናኘት ሕዝቡን ከሰፈር ይዞ ወጣ፤ ከተራራውም ግርጌ ቆሙ።

18 የሲና ተራራ እግዚአብሔር በእሳት ስለ ወረደበት በጢስ ተሸፍኖ ነበር። ጢሱ ከምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ወደ ላይ ተትጐለጐለ፤ ተራራውም በሙሉ በኀይል ተናወጠ።

19 የመለከቱም ድምፅ እያየለ መጣ። ከዚያም ሙሴ ተናገረ፤ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት።

20 እግዚአብሔር በሲና ተራራ ጫፍ ላይ ወረደ፤ ሙሴን ወደ ተራራው ጫፍ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።

21 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለማየት በመጣደፍ ብዙዎቹ እንዳይጠፉ ውረድና አስጠንቅቃቸው

22 ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡት ካህናት እንኳ ራሳቸውን መቀደስ አለባቸው፤ አለዚያ እግዚአብሔር ቍጣውን ያወርድባቸዋል።”

23 ሙሴ እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ሕዝቡ ወደ ሲና ተራራ ሊወጡ አይችሉም፤ ምክንያቱም አንተ ራስህ ‘በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ፤ የተቀደሰም በማድረግ ለየው’ በማለት አስጠንቅቀኸናልና።”

24 እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ውረድና አሮንን ከአንተ ጋራ ይዘኸው ውጣ፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን ወደ እግዚአብሔር ለመምጣት መጣደፍ የለባቸውም፤ አለዚያ እርሱ ቍጣውን ያወርድባቸዋል።”

25 ስለዚህ ሙሴ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ነገራቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告