Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 18 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ዮቶር ወደ ሙሴ መጣ

1 የምድያም ካህን የሙሴ ዐማት ዮቶር፣ እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገላቸውን ሁሉ እንዲሁም እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸው ሰማ።

2 ሙሴ ሚስቱን ሲፓራን ከመለሳት በኋላ ዐማቱ ዮቶር እርሷንና ሁለት ወንድ ልጆቿን ተቀብሏቸው ነበር።

3 ሙሴ፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ለማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ጌርሳም አለው።

4 “የአባቴ አምላክ ረዳቴ ነው፤ ከፈርዖን ሰይፍ አድኖኛልና” ለማለት ደግሞ ሁለተኛውን ልጁን አልዓዛር አለው።

5 የሙሴ ዐማት ዮቶር ከሙሴ ወንድ ልጆችና ሚስት ጋራ ሆኖ በምድረ በዳ ከእግዚአብሔር ተራራ አጠገብ ወደ ሰፈረበት ወደ ሙሴ መጣ።

6 ዮቶር ወደ ሙሴ፣ “እኔ ዐማትህ ዮቶር፣ ከሚስትህና ከሁለት ወንዶች ልጆቿ ጋራ እየመጣን ነው” ሲል መልእክት ላከበት።

7 ስለዚህ ሙሴ ዐማቱን ሊቀበለው ወጣ፤ ዝቅ ብሎ እጅ በመንሣትም ሳመው፤ ከዚያም ሰላምታ ተለዋውጠው ወደ ድንኳኑ ገቡ።

8 ሙሴም እግዚአብሔር ለእስራኤል ሲል በፈርዖንና በግብጻውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በመንገድም ላይ ስላጋጠማቸው መከራ ሁሉና እግዚአብሔርም እንዴት እንዳዳናቸው ለዐማቱ ነገረው።

9 ዮቶርም እግዚአብሔር እነርሱን ከግብጻውያን እጅ በመታደግ ለእስራኤል ያደረገውን በጎ ነገር ሁሉ በመስማቱ ተደሰተ።

10 እንዲህም አለ፤ “ከግብጻውያን እጅና ከፈርዖን ለታደጋችሁ፣ ከግብጻውያን እጅ ሕዝቡን ለታደገ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።

11 እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ በላይ ኀያል እንደ ሆነ አሁን ዐወቅሁ፤ እስራኤልን በትዕቢት ይዘው በነበሩት ሁሉ ላይ ይህን አድርጓልና።”

12 ከዚያም የሙሴ ዐማት ዮቶር የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌሎች መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ አሮንም ከሙሴ ዐማት ጋራ በእግዚአብሔር ፊት እንጀራ ለመብላት ከእስራኤል አለቆች ሁሉ ጋራ መጣ።

13 በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን ለመዳኘት ተቀመጠ፤ እነርሱም በዙሪያው ከጧት እስከ ማታ ድረስ ቆሙ።

14 ዐማቱም ሙሴ ለሕዝቡ የሚያደርገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፣ “ምን ማድረግህ ነው? እነዚህ ሁሉ ሰዎች ከጧት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመው ሳለ፣ ብቻህን በፍርድ ወንበር ላይ ለምን ትቀመጣለህ?” አለው።

15 ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ምክንያቱም ሰዎቹ የእግዚአብሔር ፈቃድ በመፈለግ ወደ እኔ ይመጣሉ።

16 ክርክር በኖራቸው ቍጥር ጕዳያቸው ወደ እኔ ይመጣል፤ ለግራና ለቀኙ የሚሆነውን እኔ ወስኜ የእግዚአብሔርን ሥርዐትና ሕጎች እነግራቸዋለሁ።”

17 የሙሴ ዐማት መልሶ እንዲህ አለው። “የምትሠራው መልካም አይደለም።

18 አንተና ወደ አንተ የሚመጡት እነዚህ ሰዎች የምታደርጉት ነገር ቢኖር ራሳችሁን ማድከም ነው፤ ሥራው ለአንተ ከባድ ሸክም ነው፤ ብቻህን ልትወጣው አትችልም።

19 ምክር እሰጥሃለሁና አሁን እኔን ስሙኝ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ይሁን። አንተ በእግዚአብሔር ፊት ሕዝብን የምትወክል መሆን አለብህ፤ ክርክራቸውን ወደ እርሱ ታቀርባለህ።

20 ሥርዐቶቹንና ሕጎቹን አስተምራቸው፤ እንዴት መኖር እንዳለባቸውና ምን መሥራት እንደሚገባቸው አሳያቸው።

21 ነገር ግን ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ከሕዝቡ ሁሉ ምረጥ፤ እነዚህም ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ታማኞችና በማታለል የሚገኘውን ጥቅም የሚጸየፉ ይሁኑ። የሺሕ፣ የመቶ፣ የዐምሳ፣ የዐሥር፣ አለቃ አድርገህ ሹማቸው።

22 በማንኛውም ጊዜ ሕዝቡን ይዳኙ፤ ቀላሉን ነገር እነርሱ ይወስኑ፤ አስቸጋሪ የሆነውን ጕዳይ ሁሉ ግን ለአንተ እንዲያቀርቡ አድርግ፤ ሥራውን ስለሚያግዙህ ሸክምህ ይቃለላል።

23 አንተ ይህን ብታደርግና እግዚአብሔርም ይህንኑ ቢያዝዝህ፣ ድካምህን መቋቋም ትችላለህ፤ እነዚህም ሰዎች ሁሉ ረክተው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።”

24 ሙሴ ዐማቱን ሰማ፤ ያለውንም ሁሉ ፈጸመ።

25 ሙሴም ከእስራኤል መካከል ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መረጠና፤ የሕዝብ መሪዎች፣ በሺሕዎች፣ በመቶዎች፣ በዐምሳዎች በዐሥሮች ላይም አለቆች አደረጋቸው።

26 ሁልጊዜም የሕዝብ ዳኞች ሆነው አገለገሉ፤ አስቸጋሪ ጕዳዮችን ወደ ሙሴ አመጡ፤ ቀላል የሆነውን ራሳቸው ወሰኑ።

27 ከዚያም ሙሴ ዐማቱን በጕዞው ሸኘው፤ ዮቶርም ወደ አገሩ ተመለሰ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告