Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 16 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መናና ድርጭት

1 መላው የእስራኤል ማኅበር ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ወር በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ከኤሊም ተነሥተው በኤሊምና በሲና መካከል ወደምትገኘው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ።

2 በምድረ በዳውም መላው የእስራኤል ልጆች ማኅበር በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ።

3 እስራኤላውያንም እነርሱን እንዲህ አሏቸው፣ “በሥጋ መቀቀያው ምንቸት ዙሪያ ተቀምጠን የፈለግነውን ያህል ምግብ መመገብ በምንችልበት በግብጽ ሳለን፣ ምነው በእግዚአብሔር እጅ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! እናንተ ግን ይህ ሁሉ ጉባኤ በራብ እንዲያልቅ ወደዚህ ምድረ በዳ አመጣችሁን” አሏቸው።

4 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ከሰማይ እንጀራ አዘንብላችኋለሁ። ሕዝቡም በየቀኑ እየወጡ ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰብስቡ፤ በዚህም ትእዛዞቼን ይጠብቁ እንደ ሆነ እፈትናቸዋለሁ።

5 በስድስተኛው ቀን በሌሎቹ ዕለታት ከሚሰበስቡት ዕጥፍ ሰብስበው ያዘጋጁ።”

6 ስለዚህ ሙሴና አሮን ለእስራኤላውያን ሁሉ፣ እንዲህ አሉ፤ “ከግብጽ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር መሆኑን በዛሬዪቱ ምሽት ታውቃላችሁ።

7 በርሱ ላይ ያሰማችሁትን ማጕረምረም ሰምቷልና በማለዳ የእግዚአብሔርን ክብር ታያላችሁ፤ ለመሆኑ በእኛስ ላይ የምታጕረመርሙት እኛ ምንድን ነንና ነው?” አሏቸው።

8 ሙሴም ንግግሩን በመቀጠል፣ “በርሱ ላይ ማጕረምረማችሁን ሰምቷልና በምሽት የምትበሉትን ሥጋ፣ በማለዳም የምትፈልጉትን ያህል እንጀራ በሚሰጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር መሆኑን ታውቃላችሁ፤ እኛ ማን ነን? በእኛ ላይ አይደለም ያጕረመረማችሁት፤ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ” አላቸው።

9 ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ ‘ማጕረምረማችሁን እርሱ ሰምቷልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ’ ብለህ ለመላው የእስራኤል ማኅበር ተናገር” አለው።

10 አሮንም ለመላው የእስራኤል ማኅበር ሲናገር ሳለ ወደ ምድረ በዳው ተመለከቱ፤ በዚያም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ላይ ተገልጦ ይታይ ነበር።

11 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

12 “የእስራኤላውያንን ማጕረምረም ሰምቻለሁ፤ ይህን ንገራቸው፤ ‘ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት ሥጋ ትበላላችሁ፤ ሲነጋም እንጀራ ትበላላችሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ”

13 በዚያች ምሽት ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤ በነጋውም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ተኝቶበት ነበር።

14 ጤዛው ከረገፈ በኋላ በሜዳው ላይ ስስ የሆነ ዐመዳይ የሚመስል የተጋገረ ነገር በምድረ በዳው ላይ ታየ።

15 እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ምን እንደ ሆነ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። ሙሴም፣ “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው አላቸው።

16 እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጎሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር አዝዟል።

17 እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ።

18 የሰበሰቡትን በጎሞር በሰፈሩ ጊዜ፣ ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አልጐደለበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ።

19 ሙሴም፣ “ማንም ከዚህ ለነገ ምንም ማስተረፍ የለበትም” አላቸው።

20 ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ሙሴ የተናገረውን ቸል በማለት ከሰበሰቡት ውስጥ ከፊሉን አስተርፈው አሳደሩ፤ በማግስቱም ጧት ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ ስለዚህ ሙሴ ተቈጣቸው።

21 በየማለዳው እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሓዩ እየበረታ በሄደም ጊዜ ቀለጠ።

22 በስድስተኛው ቀን ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ሁለት ጎሞር አድርገው ዕጥፍ ሰበሰቡ፤ የማኅበሩም አለቆች ወደ ሙሴ መጥተው ይህንኑ ነገሩት።

23 እርሱም አላቸው፤ “እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘ነገ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሰንበት በመሆን፣ የዕረፍት ቀን ይሆናል።’ ስለዚህ መጋገር የምትፈልጉትን ጋግሩ፤ መቀቀል የምትፈልጉትን ቀቅሉ። የተረፈውን አስቀምጡ፤ እስከ ጧትም ድረስ አቈዩት።”

24 ስለዚህ ሙሴ እንዳዘዘው እስከ ጧት ድረስ አቈዩት፤ አልሸተተም፤ ወይም አልተላም።

25 ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ዛሬውኑ ብሉት፤ ዛሬ የእግዚአብሔር ሰንበት ነውና። ዛሬ በመሬት ላይ ምንም አታገኙም።

26 ስድስት ቀን ትሰበስቡታላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን በሰንበት ዕለት ግን ምንም ነገር አይኖርም።”

27 ሆኖም አንዳንዶቹ በሰባተኛው ቀን ለመሰብሰብ ወጡ፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም።

28 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ትእዛዞቼንና መመሪያዎቼን ለመፈጸም እስከ መቼ እንቢ ትላላችሁ?

29 እግዚአብሔር ሰንበትን የሰጣችሁ መሆኑን ልብ በሉ፤ በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚሆን እንጀራ የሰጣችሁ ለዚህ ነው። በሰባተኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ባለበት ይቈይ፤ ማንም አይወጣም።”

30 ስለዚህ ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፉ።

31 የእስራኤልም ሕዝብ ምግቡን መና አሉት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ፣ ጣሙም ከማር እንደ ተጋገረ ቂጣ ነበር።

32 ሙሴም አለ፤ “እግዚአብሔር ያዘዘን ይህ ነው፤ ‘ከግብጽ ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ እንድትበሉ የሰጠኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ አንድ ጎሞር መና ወስደህ ለሚመጡት ትውልዶች አቈየው።’ ”

33 ስለዚህ ሙሴ አሮንን፣ “አንድ ማሰሮ ወስደህ አንድ ጎሞር መና አስቀምጥበት፤ ለሚመጡት ትውልዶች እንዲቈይም በእግዚአብሔር ፊት አስቀምጠው” አለው።

34 እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አሮን፣ መናው ይጠበቅ ዘንድ በምስክሩ ፊት አስቀመጠው።

35 እስራኤላውያን ወደ መኖሪያቸው ምድር እስኪመጡ ድረስ ለአርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ድንበር እስከሚደርሱ ድረስ መና በሉ።

36 አንድ ጎሞር የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告