ዘፀአት 13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበኵር ሁሉ ለእግዚአብሔር መቀደሱ 1 እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 2 “መጀመሪያ የተወለደውን ወንድ ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ ከእስራኤላውያን መካከል የእናቱ የበኵር ልጅ የሆነው ማሕፀን ከፋች ሰውም ሆነ እንስሳ የእኔ ነው።” 3 ከዚያም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “ከባርነት ምድር ከግብጽ የወጣችሁባትን ይህችን ዕለት አስታውሱ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ አውጥቷችኋል። እርሾ ያለበትን ማንኛውንም ነገር አትብሉ። 4 እነሆ በዚች ዕለት በአቢብ ወር ወጥታችኋል። 5 እግዚአብሔር ለእናንተ ለመስጠት ሲል ቀድሞ ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ኤዊያውያን፣ ኢያቡሳውያን ምድር በምትገቡበት ጊዜ ይህን በዓል በዚህ ወር ታከብራላችሁ። 6 ለሰባት ቀን ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በሰባተኛውም ቀን ለእግዚአብሔር በዓል ታደርጋላችሁ። 7 በእነዚህም ሦስት ቀናት ቂጣ ትበላላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ እርሾ ያለበት ነገር ፈጽሞ አይገኝ፤ በምድራችሁም አዋሳኝ በየትኛውም ቦታ እርሾ ፈጽሞ አይኑር። 8 በዚያችም ዕለት፣ ‘እኔ ይህን የማደርገው ከግብጽ ምድር በወጣሁበት ጊዜ እግዚአብሔር ስላደረገልኝ ነገር ነው’ ብለህ ለልጅህ ንገረው። 9 የእግዚአብሔር ሕግ በከንፈራችሁ ላይ እንዲሆን ይህ በዓል ለእናንተ በእጃችሁ ላይ እንደ ታሰረ ምልክት፣ በእግራችሁ ላይ እንደሚገኝ መታሰቢያ ይሆንላችኋል። እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ ከግብጽ አውጥቷችኋልና። 10 ይህን ሥርዐት በተወሰነው ጊዜ በየዓመቱ ጠብቁት። 11 “እግዚአብሔር ለእናንተና ለቀደሙት አባቶቻችሁ በመሐላ በሰጠው ተስፋ መሠረት ወደ ከነዓናውያን አገር በሚያስገባችሁና ምድሪቱንም ለእናንተ በሚሰጣችሁ ጊዜ፣ 12 የእናቱን ማሕፀን የሚከፍተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ትሰጣላችሁ፤ እንደዚሁም እንስሶቻችሁ በመጀመሪያ የወለዷቸው ወንዶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሆናሉ። 13 ከአህያ በመጀመሪያ የተወለደውን ውርንጫ ግን በጠቦት ትዋጁታላችሁ፤ አህያውን ካልዋጃችሁት ግን ዐንገቱን ስበሩት። ከወንድ ልጆቻችሁ መካከል በኵር የሆኑትን ሁሉ ዋጁ። 14 “በሚመጡት ዘመናት ልጅህ፣ ‘ይህ ምን ማለት ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ እንዲህ በለው፤ ‘ከባርነት ምድር ከግብጽ እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ አወጣን፤ 15 ፈርዖን እኛን አልለቅም ብሎ ልቡን ባደነደነ ጊዜ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ በኵር ሆኖ በግብጽ የተወለደውን ሁሉ እግዚአብሔር ገደለው። እንግዲህ በመጀመሪያ የእናቱን ማሕፀን የከፈተውን ወንድ ሁሉ ለእግዚአብሔር የምሠዋውና የልጆቼ በኵር ሆኖ የተወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ የምዋጀው በዚህ ምክንያት ነው።’ 16 እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ እኛን ከግብጽ ያወጣን ስለ ሆነ ይህ ሥርዐት በእጅህም ሆነ በግንባርህ ላይ እንደ ምልክት ይሆናል።” ቀይ ባሕርን መሻገር 17 ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ አቋራጭ ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔር በፍልስጥኤም ምድር በሚያልፈው መንገድ አልመራቸውም፤ “ጦርነት ቢያጋጥማቸው ሐሳባቸውን ለውጠው ወደ ግብጽ ይመለሱ ይሆናል” ብሏልና። 18 ስለዚህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባሕር መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብጽ ወጡ። 19 ዮሴፍ፣ “እግዚአብሔር በርግጥ ይጐበኛችኋል፤ በዚያ ጊዜም ዐፅሜን ይዛችሁ ከዚች ምድር መውጣት አለባችሁ” ብሎ የእስራኤልን ልጆች አስምሏቸው ስለ ነበር ሙሴ የዮሴፍን ዐፅም ይዞ ወጣ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባሕር መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብጽ ወጡ። 20 እነርሱም ከሱኮት ከተነሡ በኋላ ከምድረ በዳው ጥግ ባለው በኤታም ሰፈሩ። 21 ስለዚህ በቀንም ሆነ በሌሊት መጓዝ ይችሉ ዘንድ፣ እግዚአብሔር በቀን በመንገዳቸው ሊመራቸው በደመና ዓምድ፣ በሌሊት ደግሞ ብርሃን ሊሰጣቸው በእሳት ዐምድ በፊታቸው ይሄድ ነበር። 22 በቀንም ሆነ በሌሊት የደመናውና የእሳቱ ዐምድ ከሕዝቡ ፊት የተለየበት ጊዜ አልነበረም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.