Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በበኵሮች ላይ የወረደ መቅሠፍት

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በፈርዖንና በግብጽ ላይ አንድ ሌላ መቅሠፍት አወርድባቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ፈርዖን ይለቅቃችኋል፤ ሲለቅቃችሁም አንዳችሁን ሳያስቀር ያስወጣችኋል።

2 ለእስራኤል ሕዝብ፣ ለወንዶቹም ሆነ ለሴቶቹ የብርና የወርቅ ዕቃዎች ከየጎረቤቶቻቸው ስጡን ብለው እንዲወስዱ ንገራቸው።”

3 እግዚአብሔርም እስራኤላውያን በግብጻውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙ አደረጋቸው። ሙሴም በግብጽ ምድር በፈርዖን ሹማምትና በመላው ሕዝብ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ሆነ።

4 ከዚህ በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እኩለ ሌሊት ሲሆን በመላው የግብጽ ምድር ላይ ዐልፋለሁ።

5 በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን ልጅ አንሥቶ የወፍጮ መጅ ገፊ እስከ ሆነችው እስከ ባሪያዪቱ ልጅ ድረስ በግብጽ ምድር በኵር ሆኖ የተወለደ ወንድ ልጅ ሁሉ ይሞታል፤ እንዲሁም የቀንድ ከብቱ በኵር በሙሉ ያልቃል።

6 በግብጽ ምድር ሁሉ ከዚህ በፊት ያልተሰማ ወደ ፊትም የማይሰማ ታላቅ ዋይታ ይሆናል።

7 በእስራኤላውያን ዘንድ ግን በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽባቸውም።’ በዚህም እግዚአብሔር በግብጻውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት የሚያደርግ መሆኑን ታውቃላችሁ።

8 ሹማምትህ በሙሉ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ እጅ እየነሡም ‘አንተም ሆንህ የምትመራቸው ሰዎች በሙሉ ውጡልን’ ብለው ይለምኑኛል፤ እኔም ከዚያ በኋላ እሄዳለሁ።” ከዚያም ሙሴ በታላቅ ቍጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።

9 እግዚአብሔር ሙሴን “ድንቅ ሥራዎቼ በግብጽ ምድር በብዛት ይታዩ ዘንድ ፈርዖን እናንተን አይሰማችሁም” አለው።

10 ሙሴና አሮንም እነዚህን ድንቅ ታምራት በፈርዖን ፊት አደረጉ። ነገር ግን እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን ከአገሩ ለቅቀው እንዲሄዱ አልፈቀደም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告