ዘፀአት 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየአንበጣ መንጋ መቅሠፍት 1 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ተመልሰህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች በመካከላቸው ለማድረግ የፈርዖንንና የሹማምቱን ልብ አደንድኛለሁና፤ 2 ይኸውም ግብጻውያንን እንዴት አድርጌ እንደ ቀጣኋቸውና በመካከላቸውም ምልክቶቼን እንዴት እንዳደረግሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ እንድትነግሩና እኔ እግዚአብሔር መሆኔንም እንድታውቁ ነው።” 3 ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ራስህን በፊቴ ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ሕዝቤ ያመልኩኝ ዘንድ ልቀቃቸው። 4 እንዳይሄዱ ብትከለክላቸው ነገ በአገርህ ላይ አንበጣዎችን አመጣለሁ። 5 አንበጣዎቹም ምድሪቱ እስከማትታይ ድረስ ይሸፍኗታል፤ በመስክህ ላይ እያቈጠቈጠ ያለውን ዛፍ ሁሉ ሳይቀር ከበረዶ የተረፈውንም ጥቂቱን ሁሉ ይበሉታል። 6 የአንተን፣ የሹማምትህንና የግብጻውያንን ቤቶች ሁሉ ይሞሏቸዋል፤ ይህም አባቶችህም ሆኑ ቅድመ አያቶችህ በዚህች ምድር ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከቶ አይተውት የማያውቁት ነው።’ ” ሙሴም ተመለሰና ከፈርዖን ተለይቶ ሄደ። 7 የፈርዖንም ሹማምት፣ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ሰዎቹን ልቀቃቸውና ይሂዱ። ግብጽ መጥፋቷን እስካሁን አልተገነዘብህምን?” አሉት። 8 ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን እንዲመጡ ተደረገ፤ “ሂዱ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አለ። 9 ሙሴም፣ “ለእግዚአብሔር በዓል ልናከብር ስለ ሆነ ወጣቶቻችንንና ሽማግሌዎቻችንን፣ ወንድና ሴት ልጆቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ። 10 ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ከሴቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋራ እንድትሄዱ እለቅቃችኋለሁ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሁን፤ ነገር ግን ተንኰል ዐስባችኋል። 11 አይሆንም፤ ወንዶቹ ብቻ እንዲሄዱና እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አድርጉ፤ የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ሙሴና አሮን ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ። 12 እግዚአብሔር ሙሴን፣ “የአንበጣ መንጋ ምድሪቱን እንዲወርር ከበረዶ የተረፈውን ሁሉና በማሳም ላይ የበቀለውን ሁሉ ጠርጎ እንዲበላ እጅህን በግብጽ አገር ላይ ዘርጋ” አለው። 13 ስለዚህ ሙሴ በግብጽ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በዚያ ቀንና ሌሊት በሙሉ በምድሪቱ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በማግስቱም ነፋሱ አንበጣዎችን አመጣ። 14 እነርሱም ግብጽን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም። 15 ምድሩ ሁሉ ጠቍሮ እስኪጨልም ድረስ አለበሱት። ከበረዶ የተረፈውን፣ በመስክ ላይ የበቀለውንና በዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ ጠርገው በሉ። በግብጽ ምድር ሁሉ በዛፍ ላይ ወይም በተክል ላይ አንዳች ቅጠል አልተረፈም ነበር። 16 ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር በእናንተም ላይ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ 17 እንግዲህ አሁን አንድ ጊዜ ደግሞ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝና ይህን ቀሣፊ መዓት እንዲያስወግድልኝ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑልኝ።” 18 ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 19 ከዚያም እግዚአብሔር ነፋሱን ወደ ብርቱ የምዕራብ ነፋስ ለወጠው፤ ያም ነፋስ አንበጣዎቹን እየነዳ ወደ ቀይ ባሕር ከተታቸው፤ በግብጽ ምድር በየትኛውም ቦታ አንድም አንበጣ አልቀረም። 20 እግዚአብሔር ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን እንዲሄዱ አልፈቀደም። የጨለማ መቅሠፍት 21 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በግብጽ ላይ ድቅድቅ ጨለማ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው። 22 ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላው ግብጽ ላይ ለሦስት ቀናት ድቅድቅ ያለ ጨለማ ሆነ። 23 በእነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ አንዱ ሌላውን ማየት ወይም ከነበረበት ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ብርሃን ነበር። 24 ከዚያም ፈርዖን ሙሴን አስጠርቶ፣ “ሄዳችሁ እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ሳይቀሩ ዐብረዋችሁ ይሂዱ፤ በጎቻችሁ፣ ፍየሎቻችሁና የጋማ ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቅሩ” አለው። 25 ሙሴም እንዲህ አለው፤ “ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤ 26 እንስሶቻችን ሁሉ ዐብረው መሄድ አለባቸው። አንድ ሰኰና እንኳ አይቀርም። ከእንስሶቻችን መካከል ለአምላካችን ለእግዚአብሔር አምልኮ የምናቀርባቸው ይኖራሉ፤ ሆኖም እዚያ ከመድረሳችን በፊት እግዚአብሔርን ለማምለክ የምናቀርባቸው እንስሳት የትኞቹ እንደ ሆኑ አስቀድመን ለይተን ማወቅ አንችልም።” 27 ነገር ግን እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም ሕዝቡን መልቀቅ አልፈቀደም። 28 ፈርዖን ሙሴን፣ “ከፊቴ ጥፋ! ሁለተኛ እኔ ዘንድ እንዳትደርስ! ፊቴን ባየህበት በዚያ ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ” አለው። 29 ሙሴም፣ “እንዳልከው ይሁን፤ እኔም ዳግመኛ ከፊትህ አልደርስም” አለው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.