Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


እስራኤላውያን በጭቈና ሥር

1 ቤተ ሰቦቻቸውን ይዘው ከያዕቆብ ጋራ ወደ ግብጽ የሄዱት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፦

2 ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣

3 ይሳኮር፣ ዛብሎን፣ ብንያም፣

4 ዳን፣ ንፍታሌም፣ ጋድና አሴር።

5 የያዕቆብ ዘር ጠቅላላ ብዛት ሰባ ሲሆን፣ ዮሴፍ ግን ቀደም ብሎ በግብጽ ነበረ።

6 ከጊዜ በኋላ ዮሴፍና ወንድሞቹ ያም ትውልድ በሙሉ ሞቱ፤

7 ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እየተዋለዱ በዙ፤ ቍጥራቸው እጅግ ከመጨመሩም የተነሣ የግብጽን ምድር ሞሏት።

8 በግብጽም፣ ስለ ዮሴፍ የማያውቅ አዲስ ንጉሥ ነገሠ።

9 እርሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ እስራኤላውያን በቍጥር በልጠውናል፤ ከእኛም ይልቅ እየበረቱ ነው፤

10 ቍጥራቸው እንዳይጨምር፣ ጦርነት ቢነሣ ከጠላቶቻችን ጋራ ዐብረው እንዳይወጉንና ከምድሪቱም ኰብልለው እንዳይሄዱ ዘዴ እንፈልግ።”

11 ስለዚህ እያስጨነቁ የግዳጅ ሥራ የሚያሠሯቸውን አሠሪ አለቆች ሾሙባቸው። እስራኤላውያንም ፊቶምና ራምሴ የተባሉ ንብረት ማከማቻ ከተሞችን ለፈርዖን ሠሩለት።

12 ነገር ግን ባስጨነቋቸው መጠን የእስራኤላውያን ቍጥር በዛ፤ በምድሪቱም እየተስፋፉ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሣ ግብጻውያኑ እስራኤላውያንን እጅግ ፈሯቸው፤

13 ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታም ያሠሯቸው ጀመር።

14 ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በዕርሻም ሁሉ እያስጨነቁ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን አስመረሩ፤ ግብጻውያኑ በሚያሠሯቸው ከባድ ሥራ ሁሉ ፈጽሞ አይራሩላቸውም ነበር።

15 የግብጽም ንጉሥ ሲፓራና ፉሐ የተባሉትን ዕብራውያን ሴቶች አዋላጆች እንዲህ አላቸው፤

16 “የዕብራውያንን ሴቶች በማማጫው ድንጋይ ላይ በምታዋልዱበት ጊዜ የሚወለደው ሕፃን ወንድ ከሆነ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።”

17 አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ የግብጽ ንጉሥ ያዘዛቸውን አልፈጸሙም፤ ወንዶቹንም ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው።

18 ንጉሡም አዋላጆቹን ጠርቶ፣ “ለምንድን ነው ወንዶቹን ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ የተዋችኋቸው?” አላቸው።

19 እነርሱም፣ “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብጻውያን ሴቶች አይደሉም፤ ብርቱዎች ስለ ሆኑ አዋላጆች ከመድረሳቸው በፊት ይወልዳሉ” ሲሉ ለፈርዖን መለሱለት።

20 ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ለአዋላጆቹ መልካም ሆነላቸው፤ ሕዝቡም በቍጥር እየበዛና እያየለ ሄደ።

21 አዋላጆቹም እግዚአብሔርን በመፍራታቸው ቤተ ሰብ ሰጣቸው።

22 ፈርዖንም፣ “የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ አባይ ወንዝ ውስጥ ጣሉት፤ ሴት ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት ትኑር” ሲል ሕዝቡን አዘዘ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告