አስቴር 7 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሐማ ተሰቀለ 1 ስለዚህ ንጉሡና ሐማ ከንግሥት አስቴር ጋራ ለመጋበዝ ሄዱ፤ 2 በሁለተኛውም ቀን የወይን ጠጅ እየጠጡ ሳለ፣ ንጉሡ እንደ ገና፣ “ንግሥት አስቴር ሆይ፤ የምትለምኚው ምንድን ነው? ይሰጥሻል፤ የምትጠይቂውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል” አላት። 3 ከዚያም ንግሥት አስቴር እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ንጉሥ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼና ግርማዊነትህን ደስ የሚያሰኝ ከሆነ፣ ሕይወቴን ታደጋት፤ ልመናዬ ይህ ነው፤ ሕዝቤን አትርፍ፤ ጥያቄዬም ይኸው ነው። 4 እኔና ሕዝቤ ለጥፋት፣ ለዕርድና ለመደምሰስ ተሸጠናልና። ወንዶችና ሴቶች ባሮች ለመሆን የተሸጥን ቢሆን ኖሮ፣ ዝም ባልሁ ነበር፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ጭንቀት ንጉሡን ለማስቸገር የሚበቃ አይደለም።” 5 ንጉሥ ጠረክሲስም ንግሥት አስቴርን፣ “ለመሆኑ እርሱ ማን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ እስከዚህ የደፈረውስ ሰው የታለ?” ሲል ጠየቀ። 6 አስቴርም፣ “ያ ባላጋራና ጠላት ይህ ክፉው ሐማ ነው” አለች። ከዚያም ሐማ በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት እጅግ ደነገጠ። 7 ንጉሡ ከተቀመጠበት በቍጣ ተነሣ፤ የወይን ጠጁንም ትቶ ወደ ቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ሄደ። ሐማ ግን ንጉሡ ሊያጠፋው ቈርጦ መነሣቱን ስላወቀ፣ ንግሥት አስቴር ሕይወቱን እንድታተርፍለት ለመማጠን በዚያው ቀረ። 8 ንጉሡ ከቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ወደ ግብዣው አዳራሽ ሲመለስ አስቴር ደገፍ ባለችበት ድንክ ዐልጋ ላይ ሐማ ተደፍቶ ነበር። ንጉሡም፣ “ይባስ ብሎ ዐብራኝ ያለችውን ንግሥት በገዛ ቤቴ ሊደፍራት ያስባልን?” ሲል ተናገረ። ይህ ቃል ከንጉሡ አፍ ገና እንደ ወጣ፣ የሐማን ፊት ሸፈኑት። 9 ከዚያም ንጉሡን በቅርብ ከሚያገለግሉት ጃንደረቦች አንዱ የሆነው ሐርቦና፣ “እነሆ ቁመቱ ዐምሳ ክንድ የሆነ ግንድ በሐማ ቤት አጠገብ ተተክሏል፤ ይህን ያዘጋጀው ንጉሡን ለማዳን በጎ ነገር ለተናገረው ለመርዶክዮስ ነው” አለ። ንጉሡም፣ “በዚሁ ላይ ስቀሉት” አለ። 10 ስለዚህ ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ ሐማን ሰቀሉት፤ ከዚያም የንጉሡ ቍጣ በረደ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.