Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

አስቴር 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


አስቴር ለንጉሡ ያቀረበችው ልመና

1 በሦስተኛው ቀን አስቴር የክብር ልብሷን ለብሳ በንጉሡ አዳራሽ ፊት ለፊት ባለው በቤተ መንግሥቱ ውስጠኛ አደባባይ ገብታ ቆመች። ንጉሡም አዳራሹ ውስጥ በመግቢያው ትይዩ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር።

2 ንግሥት አስቴር በአደባባዩ ላይ ቆማ ሲያያት ደስ አለው፤ በእጁ የያዘውን የወርቅ ዘንግ ዘረጋላት፤ አስቴርም ቀረብ ብላ የዘንጉን ጫፍ ነካች።

3 ከዚያም ንጉሡ፣ “ንግሥት አስቴር ሆይ፤ ለምን መጣሽ? ከእኔ የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይሰጥሻል” አላት።

4 አስቴርም መልሳ፣ “ንጉሡን ደስ የሚያሠኘው ቢሆን፣ ባዘጋጀሁለት ግብዣ ላይ ንጉሡ ዛሬ ከሐማ ጋራ ይገኝልኝ” አለች።

5 ንጉሡም፣ “አስቴር ያለችውን እንድንፈጽም፣ ሐማን በፍጥነት ጥሩት” አለ። ስለዚህ ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ሄዱ።

6 የወይን ጠጅ እየጠጡ ሳለ ንጉሡ ዳግመኛ አስቴርን፣ “እስኪ የምትፈልጊው ምንድን ነው? ይሰጥሻል፤ ደግሞስ የምትጠይቂው ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይፈቀድልሻል” አላት።

7 አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ልመናዬም፣ ጥያቄዬም ይህ ነው፤

8 በንጉሡ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁና የምፈልገውን ሊሰጠኝና ልመናዬንም ሊፈጽምልኝ ንጉሡን ደስ ካሠኘው፣ ንጉሡና ሐማ በማዘጋጅላቸው ግብዣ ላይ ነገ ይገኙልኝ። ከዚያም እኔ ለንጉሡ ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ።”


ሐማ በመርዶክዮስ ላይ ያወረደው ቍጣ

9 ሐማ በዚያ ቀን ደስ ብሎትና መንፈሱ ረክቶ ወጣ፤ ነገር ግን መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ሲያየው ከተቀመጠበት አለመነሣቱንና በፊቱም አለመንቀጥቀጡን ሲመለከት፣ ቍጣው በመርዶክዮስ ላይ ነደደ።

10 ሐማ ግን እንደ ምንም ራሱን ተቈጣጥሮ ወደ ቤቱ ሄደ። ወዳጆቹንና ሚስቱን ዞሳራን አስጠርቶ በአንድነት ከሰበሰባቸው በኋላ፣

11 ሐማ ስለ ሀብቱ ታላቅነት፣ ስለ ልጆቹ ብዛት እንዲሁም ንጉሡ የቱን ያህል እንዳከበረው፣ ከሌሎቹም መኳንንትና ሹማምት ይበልጥ እንዴት ከፍ ከፍ እንዳደረገው እያጋነነ ነገራቸው።

12 ሐማም፣ “ምን ይህ ብቻ” አለ፤ “ንግሥት አስቴር ባዘጋጀችው ግብዣ ላይ ከንጉሡ ጋራ እንድገኝ የጋበዘችው ሰው አንድ እኔ ብቻ ነኝ፤ ነገም ከንጉሡ ጋራ ጋብዛኛለች።

13 ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ላይ ተቀምጦ ካየሁት ይህ ሁሉ እኔን ደስ አያሠኘኝም።”

14 ሚስቱ ዞሳራና ወዳጆቹ በሙሉ፣ “ቁመቱ ዐምሳ ክንድ የሆነ መስቀያ አስተክልና መርዶክዮስ እንዲሰቀልበት በጧት ለንጉሡ ንገረው፤ ከዚያም ደስ ብሎህ ከንጉሡ ጋራ ወደ ግብዣው ግባ” አሉት። ይህም ሐሳብ ሐማን እጅግ ደስ አሠኘው፤ መስቀያውንም አስተከለ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告