Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መክብብ 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሁሉም የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ

1 ስለዚህ ይህን ሁሉ በልቤ አስቤ እንዲህ አልሁ፤ ጻድቃንና ጠቢባን የሚሠሩትም ሥራ በአምላክ እጅ ነው፤ ነገር ግን ፍቅር ይሁን ወይም ጥላቻ የሚጠብቀውን ማንም አያውቅም።

2 ጻድቃንና ኃጥኣን፣ ደጎችና ክፉዎች፣ ንጹሓንና ርኩሳን፣ መሥዋዕት የሚያቀርቡና የማያቀርቡ፣ የሁሉም የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ አንድ ነው። ለደጉ ሰው እንደ ሆነው ሁሉ፣ ለኀጢአተኛውም እንዲሁ ነው፤ ለሚምሉት እንደ ሆነው ሁሉ፣ መሐላን ለሚፈሩትም እንዲሁ ነው።

3 ከፀሓይ በታች በሁሉም ላይ የሚሆነው ክፋት ይህ ነው፤ የሁሉም የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ አንድ ነው። በዚህም ላይ የሰዎች ልብ በክፋት የተሞላ ነው፤ በሕይወት እያሉም በልባቸው ውስጥ እብደት አለ፤ በመጨረሻም ወደ ሙታን ይወርዳሉ።

4 በሕያዋን መካከል ያለ ማንኛውም ሰው ተስፋ አለው፤ በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና!

5 ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤ መታሰቢያቸው ይረሳል፤ ምንም ዋጋ የላቸውም።

6 ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸው፣ ቅናታቸውም ከጠፋ ቈይቷል፤ ከፀሓይ በታች በሚሆነው ነገር ሁሉ፣ ፈጽሞ ዕጣ ፈንታ አይኖራቸውም።

7 ሂድ፤ ምግብህን በደስታ ብላ፤ ወይንህንም ልብህ ደስ ብሎት ጠጣ፤ ባደረግኸው ነገር አምላክ ደስ ብሎታልና።

8 ዘወትር ልብስህ ነጭ ይሁን፤ ራስህንም ዘወትር በዘይት ቅባ።

9 አምላክ ከፀሓይ በታች በሰጠህ በዚህ ትርጕም የለሽ የሕይወት ዘመን ሁሉ፣ ከንቱ በሆኑትም ቀኖችህ ሁሉ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋራ ደስ ይበልህ፤ በሕይወትህና ከፀሓይ በታች በምትደክምበት ነገር ሁሉ ይህ ዕድል ፈንታህ ነውና።

10 እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው፤ ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።

11 ሌላም ነገር ከፀሓይ በታች አየሁ፤ ሩጫ ለፈጣኖች፣ ውጊያም ለኀያላን አይደለም፤ እንጀራ ለጥበበኞች፣ ወይም ባለጠግነት ለብልኆች፣ ወይም ሞገስ ለዐዋቂዎች አይሆንም፤ ጊዜና ዕድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።

12 ደግሞም የራሱን ጊዜ የሚያውቅ ሰው የለም፤ ዓሦች በክፉ መረብ እንደሚያዙ፣ ወይም ወፎች በወጥመድ እንደሚጠመዱ፣ ሰዎችም ሳያስቡት በሚመጣባቸው፣ በክፉ ጊዜ ይጠመዳሉ።


ጥበብ ከሞኝነት ይበልጣል

13 እንዲሁም እጅግ ያስገረመኝን ይህን የጥበብ ምሳሌ ከፀሓይ በታች አየሁ፤

14 ጥቂት ሰዎች የሚኖሩባት አንዲት ትንሽ ከተማ ነበረች፤ አንድ ኀያል ንጉሥም መጣባት፤ ከበባት፤ በላይዋም ትልቅ ምሽግ ሠራባት።

15 በዚያችም ከተማ ጥበበኛ የሆነ አንድ ድኻ ሰው ይኖር ነበር፤ በጥበቡም ከተማዋን አዳናት፤ ነገር ግን ያን ድኻ ማንም አላስታወሰውም።

16 ስለዚህ፣ “ጥበብ ከኀይል ይበልጣል” አልሁ፤ ሆኖም የድኻው ጥበብ ተንቋል፤ ቃሉም አልተሰማም።

17 ሞኞችን ከሚያስተዳድር ገዥ ጩኸት ይልቅ፣ ጠቢብ በዝግታ የሚናገረው ቃል ይደመጣል።

18 ጥበብ ከጦር መሣሪያ ይበልጣል፤ ነገር ግን አንድ ኀጢአተኛ ብዙ መልካም ነገርን ያጠፋል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告