መክብብ 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእግዚአብሔርን ፍራ 1 ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ። ለመስማት መቅረብ የሞኞችን መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል፤ እነርሱ ክፉ እንደሚሠሩ አያውቁምና። 2 በአፍህ አትፍጠን፤ በአምላክም ፊት ማንኛውንም ነገር ለመናገር፣ በልብህ አትቸኵል፤ አምላክ በሰማይ፣ አንተ ደግሞ በምድር ነህ፤ ስለዚህ ቃልህ ጥቂት ይሁን። 3 በሥራ ብዛት ሕልም እንደሚታይ፣ ብዙ ቃል ባለበትም የሞኝ ንግግር ይገለጣል። 4 ለአምላክ ስእለትን በተሳልህ ጊዜ ለመፈጸም አትዘግይ፤ በሞኞች ደስ አይለውምና፤ ስእለትህን ፈጽም። 5 ስእለት ተስሎ ካለመፈጸም፣ አለመሳል ይሻላል። 6 አንደበትህ ወደ ኀጢአት እንዲመራህ አትፍቀድ፤ ለቤተ መቅደስ መልእክተኛም፣ “የተሳልሁት በስሕተት ነበር” አትበል። አምላክ በተናገርኸው ተቈጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ? 7 ብዙ ሕልምና ብዙ ቃል ከንቱ ነው፤ ስለዚህ አምላክን ፍራ። ባለጠግነት ከንቱ ነው 8 በአገር ውስጥ ድኻ ተጨቍኖ፣ ፍትሕ ተጓድሎ፣ መብትም ተረግጦ ብታይ፣ እንደነዚህ ባሉ ነገሮች አትደነቅ፤ ምክንያቱም አንዱን አለቃ የበላዩ ይመለከተዋል፤ በእነዚህ በሁለቱም ላይ ሌሎች ከፍ ያሉ አሉ። 9 ከምድሩ የሚገኘው ትርፍ ለሁሉም ነው፤ ንጉሡም ራሱ የሚጠቀመው ከዕርሻ ነው። 10 ገንዘብን የሚወድድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድድ፣ በትርፉ አይረካም፤ ይህም ከንቱ ነው። 11 ሀብት በበዛ ቍጥር፣ ተጠቃሚውም ይበዛል፤ በዐይኑ ብቻ ከማየት በቀር ታዲያ፣ ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል? 12 ጥቂትም ይሁን ብዙ ቢበላ፣ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ የሀብታም ሰው ብልጽግና ግን እንቅልፍ ይነሣዋል። 13 ከፀሓይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፦ ይህም ለባለቤቱ ጕዳት የተከማቸ ሀብት፣ 14 ወይም በአንድ መጥፎ አጋጣሚ የጠፋ ብልጽግና ነው፤ ልጅ ሲወልድም፣ ለርሱ የሚያስቀርለት ምንም ነገር አይኖርም። 15 ሰው ከእናቱ ማሕፀን ዕራቍቱን ይወለዳል፤ እንደ መጣው እንዲሁ ይመለሳል። ከለፋበትም ነገር፣ አንድም እንኳ በእጁ ይዞ ሊሄድ አይችልም። 16 ይህ ደግሞ እጅግ ክፉ ነገር ነው፤ ሰው እንደ መጣ እንዲሁ ይሄዳል፤ የሚደክመው ለነፋስ ስለ ሆነ፣ ትርፉ ምንድን ነው? 17 በብዙ ጭንቀት፣ መከራና ብስጭት፣ ዘመኑን ሁሉ በጨለማ ውስጥ ይበላል። 18 የሰው ዕጣው ይህ ስለ ሆነ፣ አምላክ በሰጠው በጥቂት ዘመኑ ከፀሓይ በታች በሚደክምበት ነገር ርካታን ያገኝ ዘንድ፣ መብላቱና መጠጣቱም መልካምና ተገቢ መሆኑን ተገነዘብሁ። 19 አምላክ ለሰው ባለጠግነትና ሀብት መስጠቱ፣ እንዲደሰትበትም ማስቻሉ፣ ዕጣውን እንዲቀበልና በሥራውም እንዲደሰት ማድረጉ፣ ይህ የአምላክ ስጦታ ነው። 20 አምላክ የልብ ደስታ ስለሚሰጠውም በሕይወቱ ዘመን ያሉትን ቀናት እምብዛም አያስባቸውም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.