መክብብ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምለሁሉም ጊዜ አለው 1 ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው፤ 2 ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለመንቀልም ጊዜ አለው፤ 3 ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለማዳንም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፤ ለመገንባትም ጊዜ አለው፤ 4 ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ ለሐዘን ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም ጊዜ አለው፤ 5 ድንጋይ ለመጣል ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፤ ለመለያየትም ጊዜ አለው፤ 6 ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ለመተው ጊዜ አለው፤ ለማስቀመጥ ጊዜ አለው፤ አውጥቶ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ 7 ለመቅደድ ጊዜ አለው፤ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ 8 ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፤ ለሰላምም ጊዜ አለው። 9 ሠራተኛ ከጥረቱ የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው? 10 ሰዎች ይደክሙበት ዘንድ አምላክ የሰጣቸውን ከባድ የሥራ ጫና አየሁ። 11 ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ አምላክ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም። 12 ለሰዎች፣ በሕይወት እያሉ ደስ ከመሠኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። 13 ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የአምላክ ችሮታ ነው። 14 አምላክ ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንደሚኖር ዐውቃለሁ፤ በርሱ ላይ ምንም አይጨመርም፤ ከርሱም ምንም አይቀነስም፤ ሰዎች ይፈሩት ዘንድ ይህን አደረገ። 15 አሁን ያለው ከዚህ በፊት የነበረው ነው፤ ወደ ፊት የሚሆነውም ቀድሞ የነበረ ነው፤ አምላክም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል። 16 ከፀሓይ በታችም ሌላ ነገር አየሁ፤ በፍርድ ቦታ ዐመፅ ነበር፤ በፍትሕ ቦታ ግፍ ነበር። 17 እኔም በልቤ፣ “ለማንኛውም ድርጊት፣ ለማንኛውም ተግባር ጊዜ ስላለው፣ አምላክ ጻድቁንና ኀጢአተኛውን ወደ ፍርድ ያመጣቸዋል” ብዬ አሰብሁ። 18 እንዲህም ብዬ አሰብሁ፤ “ሰዎች፣ እንደ እንስሳት መሆናቸውን ያዩ ዘንድ አምላክ ይፈትናቸዋል። 19 የሰው ዕድል ፈንታ እንደ እንስሳት ነው፤ ሁለቱም ዕጣ ፈንታቸው አንድ ነው፤ አንዱ እንደሚሞት፣ ሌላውም እንዲሁ ይሞታል። ሁሉ አንድ ዐይነት እስትንፋስ አላቸው፤ ሰውም ከእንስሳ ብልጫ የለውም፤ ሁሉም ከንቱ ነው። 20 ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ፤ ሁሉም ከዐፈር እንደ ሆኑ፣ ተመልሰው ወደ ዐፈር ይሄዳሉ። 21 የሰው መንፈስ ወደ ላይ መውጣቱን፣ የእንስሳ እስትንፋስ ደግሞ ወደ ታች ወደ ምድር መውረዱን ማን ያውቃል?” 22 ስለዚህ ለሰው ዕጣ ፈንታው ስለ ሆነ፣ በሥራው ከመደሰት የተሻለ ነገር እንደሌለው አየሁ፤ ከርሱ በኋላ የሚሆነውንስ ተመልሶ እንዲያይ የሚያደርገው ማን ነው? |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.