ዘዳግም 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእግዚአብሔርን አትርሳ 1 በሕይወት እንድትኖሩ፣ እንድትበዙና እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በመሐላ ተስፋ የገባላቸውን ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፣ ዛሬ እኔ የምሰጥህን እያንዳንዱን ትእዛዝ ለመከተል ጥንቃቄ አድርጉ። 2 አምላክህ እግዚአብሔር ትእዛዞቹን መጠበቅህንና በልብህ ያለውን ለማወቅ፣ ትሑት ሊያደርግህና ሊፈትንህ በእነዚህ አርባ ዓመታት በዚህ ምድረ በዳ ጕዞህ ሁሉ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ። 3 ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው በእያንዳንዱ ቃል እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ሊያስተምርህ አስራበህ፤ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቁትን መና መገበህ፤ 4 በእነዚህ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብስህ አላለቀም፤ እግርህም አላበጠም። 5 ስለዚህ ሰው ልጁን እንደሚቀጣ፣ አምላክህ እግዚአብሔርም አንተን እንደሚቀጣህ በልብህ ዕወቅ። 6 በመንገዶቹ በመሄድና እርሱንም በማክበር፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ጠብቅ። 7 አምላክህ እግዚአብሔር ጅረቶችና የኵሬ ውሃ ወዳለበት፣ ምንጮች ከየሸለቆውና ከየኰረብታው ወደሚፈስሱበት ወደ መልካሚቱ ምድር ያገባሃል፣ 8 ስንዴና ገብስ፣ ወይንና የበለስ ዛፎች፣ ሮማን፣ የወይራ ዘይትና ማር የሚገኝባት ምድር፤ 9 ምንም ነገር የማይታጣባት፣ የዳቦም ዕጦት የሌለባት፣ ዐለቶች ብረት የሆኑባት፣ ከኰረብቶቿም መዳብ ቈፍረህ ልታወጣ የምትችልባት ምድር ናት። 10 በልተህ በምትጠግብበት ጊዜ እንዲህ ያለች መልካም ምድር ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን ባርከው። 11 በዛሬዪቱ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሕጉንና ሥርዐቱን ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳው ተጠንቀቅ። 12 አለዚያ በልተህ ስትጠግብና ጥሩ ጥሩ ቤቶችን ሠርተህ መኖር ስትጀምር፣ 13 ደግሞም የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህ ሲበዛ፣ ብርህና ወርቅህ ሲበረክት፣ ያለህም ሁሉ በላይ በላዩ እየጨመረ ሲሄድ፣ 14 ልብህ ይታበይና ከባርነት ምድር፣ ከግብጽ ያወጣህን አምላክህን እግዚአብሔርን ትረሳለህ። 15 በዚያ ጭልጥ ባለና አስፈሪ ምድረ በዳ፣ በዚያ በሚያስጠማና ውሃ በማይገኝበት ደረቅ መሬት፣ መርዘኛ እባብና ጊንጥ ባለበት ምድረ በዳ መራህ፤ ከጽኑ ዐለትም ውሃ አፈለቀልህ። 16 በመጨረሻ መልካም እንዲሆንልህ፣ አንተን ትሑት ለማድረግና ለመፈተን፣ አባቶችህ ፈጽሞ የማያውቁትን መና በምድረ በዳ መገበህ። 17 ምናልባትም፣ “ይህን ሀብት ያፈራሁት በጕልበቴና በእጄ ብርታት ነው” ብለህ በልብህ ታስብ ይሆናል። 18 ነገር ግን ሀብት እንድታፈራ ችሎታ የሰጠህ፣ ለአባቶችህም በመሐላ የገባውን ኪዳን ያጸናልህ እርሱ ስለ ሆነ፣ አምላክህን እግዚአብሔርን ዐስበው። 19 አምላክህን እግዚአብሔርን ብትረሳና ሌሎችን አማልክት ብትከተል፣ ብታመልክና ለእነርሱ ብትሰግድላቸው በርግጥ እንደምትጠፉ ዛሬ እመሰክርባችኋለሁ። 20 እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያሉትን አሕዛብ እንዳጠፋቸው ሁሉ፣ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛችሁ እናንተም ትጠፋላችሁ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.