Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘዳግም 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ዐሥርቱ ትእዛዛት
5፥6-21 ተጓ ምብ – ዘፀ 20፥1-17

1 ሙሴ እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ እስራኤል ሆይ፤ በዛሬዋ ዕለት በጆሯችሁ የምነግራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ አጥኗቸው፤ በጥንቃቄም ጠብቋቸው።

2 አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋራ ቃል ኪዳን ገብቷል።

3 እግዚአብሔር ይህን ቃል ኪዳን የገባውም ከአባቶቻችን ጋራ ሳይሆን፣ ዛሬ እዚህ በሕይወት ከምንገኘው ከእኛ ከሁላችን ጋራ ነው።

4 እግዚአብሔር እናንተን በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ፊት ለፊት አነጋገራችሁ።

5 እናንተ ግን እሳቱን በመፍራት ወደ ተራራው ስላልወጣችሁ፣ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ለእናንተ እነግራችሁ ዘንድ እኔ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል ቆምሁ። እርሱም እንዲህ አለ፤

6 “ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።

7 “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።

8 በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም ከምድር በታች ወይም ውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ነገሮች በማናቸውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ፤

9 አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸውም፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር፣ የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።

10 ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺሕ ትውልድ ፍቅርን የማሳይ ነኝ።

11 የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አታንሣ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚያነሣውን በደል አልባ አያደርገውምና።

12 አምላክህ እግዚአብሔር ባዘዘህ መሠረት የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ አክብረው።

13 ስድስት ቀን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አከናውን።

14 ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። በዚያ ቀን አንተም ሆንህ ወንድ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ በሬህ፣ አህያህ ወይም ማንኛውም እንስሳህ ወይም ደግሞ በደጅህ ያለ እንግዳ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ። ይህም አንተ እንዳረፍህ ሁሉ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ እንዲያርፉ ነው።

15 በግብጽ ሳለህ አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ፤ ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ።

16 አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝምና መልካም እንዲሆንልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ባዘዘህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር።

17 አትግደል።

18 አታመንዝር።

19 አትስረቅ።

20 በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።

21 የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ። በባልንጀራህ ቤትም ሆነ በመሬቱ፣ በወንድ ሆነ በሴት አገልጋዩ፣ በበሬውም ሆነ በአህያው ወይም የርሱ በሆነው በማንኛውም ነገር ላይ ዐይንህን አትጣል።”

22 እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳቱ፣ በደመናውና በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ለማኅበራችሁ ሁሉ በከፍተኛ ድምፅ የተናገራችሁ ትእዛዞቹ እነዚህ ናቸው፤ የጨመረውም ሌላ የለም፤ ትእዛዞቹንም በሁለት የድንጋይ ጽላት ላይ ጽፎ ሰጠኝ።

23 ተራራው በእሳት ሲቃጠል፣ ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ፣ እናንተ የየነገዶቻችሁ አለቆችና ሽማግሌዎቻችሁም በሙሉ ወደ እኔ ዘንድ መጣችሁ፤

24 እንዲህም አላችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር ክብሩንና ግርማውን አሳይቶናል፤ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል። እግዚአብሔር አነጋግሮትም እንኳ፣ ሰው በሕይወት ሊኖር እንደሚችል በዛሬው ቀን አይተናል።

25 ከእንግዲህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ድምፅ ብንሰማ እንሞታለን፤ ይህችም ታላቅ እሳት ፈጽማ ታጠፋናለች፤ ታዲያ ለምን እንሙት?

26 ለመሆኑ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር እኛ እንደ ሰማነው ሁሉ፣ የሕያው እግዚአብሔርን ድምፅ ሰምቶ በሕይወት ለመኖር የቻለ ከሥጋ ለባሽ ማን አለ?

27 አንተ ቅረብ፤ አምላካችን እግዚአብሔር የሚለውን ሁሉ ስሙ፤ ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር የሚነግርህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እንሰማለን፤ እናደርገዋለንም።”

28 ይህን ስትነግሩኝ እግዚአብሔር ሰማ፤ እግዚአብሔርም አለኝ፤ “ይህ ሕዝብ ምን እንዳለህ ሰምቻለሁ፤ ያሉትም ሁሉ መልካም ነው።

29 ታዲያ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም እንዲሆንላቸው፣ እኔን እንዲፈሩና ሁልጊዜ ትእዛዞቼን ሁሉ እንዲጠብቁ እንደዚህ ያለ ልብ ቢኖራቸው ምናለ!

30 “ሄደህ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ ንገራቸው።

31 አንተ ግን እንዲወርሷት በምሰጣቸው ምድር እንዲጠብቋቸው የምታስተምራቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ሕጎች ሁሉ እንድሰጥህ እዚሁ ከእኔ ዘንድ ቈይ።”

32 እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ለመፈጸም ተጠንቀቁ፤ ቀኝም ግራም አትበሉ።

33 በምትወርሷት ምድር በሕይወት ለመኖር እንድትችሉ፣ መልካም እንዲሆንላችሁና ዕድሜያችሁም እንዲረዝም፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告