Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘዳግም 34 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሙሴ መሞት

1 ሙሴ ከሞዓብ ሜዳ ተነሥቶ ለኢያሪኮ ትይዩ ወደ ሆነው ፈስጋ ጫፍ፣ ወደ ናባው ተራራ ወጣ። በዚያም እግዚአብሔር ምድሪቱን ሁሉ አሳየው፤ ይኸውም ከገለዓድ እስከ ዳን፣

2 ንፍታሌምን ሁሉ፣ የኤፍሬምንና የምናሴን ግዛት፣ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ ያለውን የይሁዳን ምድር ሁሉ፣

3 ኔጌብንና የዘንባባ ከተማ ከሆነችው ከኢያሪኮ ሸለቆ እስከ ዞዓር ያለውን ምድር ሁሉ ነው።

4 ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ፣ ‘ለዘሮቻችሁ እሰጣለሁ’ ብዬ በመሐላ ቃል የገባሁላቸው ምድር ይህች ናት። በዐይንህ እንድታያት አድርጌአለሁ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትሻገርም” አለው።

5 እግዚአብሔር እንደ ተናገረው የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በሞዓብ ምድር ሞተ።

6 በሞዓብ ምድር በቤተ ፌጎር ፊት ለፊት ባለው ሸለቆ ቀበረው፤ ይሁን እንጂ መቃብሩ የት እንደ ሆነ እስከ ዛሬ ማንም አያውቅም።

7 ሙሴ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሃያ ዓመት ነበር፤ ሆኖም ዐይኑ አልፈዘዘም፤ ጕልበቱም አልደከመም።

8 የልቅሶውና የሐዘኑ ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ፣ እስራኤላውያን ለሙሴ በሞዓብ ሜዳ ሠላሳ ቀን አለቀሱለት።

9 ሙሴ እጆቹን ጭኖበት ነበርና፣ የነዌ ልጅ ኢያሱ በጥበብ መንፈስ ተሞላ። ስለዚህ እስራኤላውያን አደመጡት፤ እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞት የነበረውንም ሁሉ አደረጉ።

10 እግዚአብሔር ፊት ለፊት ያወቀው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ ከዚያ ወዲህ በእስራኤል አልተነሣም።

11 እግዚአብሔር ልኮት፣ እነዚያን ታምራዊ ምልክቶችና ድንቆች ሁሉ በግብጽ በፈርዖን፣ በሹማምቱና በምድሪቱ ሁሉ ላይ እንዲያደርግ የላከውን ያደረገ ማንም ሰው አልነበረም።

12 ሙሴ በእስራኤል ሁሉ ፊት ያሳየውን ታላቅ ኀይል ያሳየ ወይም ያደረገውን አስፈሪ ተግባር የፈጸመ ማንም ሰው የለም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告