Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘዳግም 29 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የቃል ኪዳኑ መታደስ

1 እግዚአብሔር በኮሬብ ከገባው ቃል ኪዳን በተጨማሪ በሞዓብ ምድር ከእስራኤላውያን ጋራ እንዲያደርግ ሙሴን ያዘዘው የኪዳኑ ቃሎች እነዚህ ናቸው።

2 ሙሴ እስራኤላውያንን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ እግዚአብሔር በግብጽ፣ በፈርዖን፣ በሹማምቱ ሁሉና በመላ አገሩ ላይ ያደረገውን ሁሉ ዐይኖቻችሁ አይተዋል።

3 እነዚያን ከባድ ፈተናዎች፣ ታምራዊ ምልክቶችና ታላላቅ ድንቆች በገዛ ዐይኖቻችሁ አይታችኋል።

4 ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሔር የሚያስተውል አእምሮ ወይም የሚያይ ዐይን ወይም የሚሰማ ጆሮ አልሰጣችሁም።

5 በምድረ በዳ በመራኋችሁ በእነዚያ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብሳችሁ አላረጀም፤ የእግራችሁም ጫማ አላለቀም።

6 ቂጣ አልበላችሁም፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣችሁም፤ ይህን ያደረግሁት እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ ነው።

7 ወደዚህ ስፍራ በደረሳችሁ ጊዜ፣ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎንና የባሳን ንጉሥ ዐግ ሊወጉን መጡ፤ ሆኖም ድል አደረግናቸው።

8 ምድራቸውንም ወስደን ለሮቤላውያን፣ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠን።

9 እንግዲህ የምታደርጉት ሁሉ እንዲከናወንላችሁ፣ የዚህን ኪዳን ቃሎች በጥንቃቄ ተከተሉ።

10 እናንተ ሁላችሁ መሪዎቻችሁና አለቆቻችሁ፣ ሽማግሌዎቻችሁና ሹሞቻችሁ እንዲሁም ሌሎች የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቆማችኋል፤

11 ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ ዕንጨትህን እየፈለጡ፣ ውሃህንም እየቀዱ በሰፈርህ የሚኖሩ መጻተኞችም ዐብረውህ ቆመዋል።

12 እዚህ የቆምኸው እግዚአብሔር ዛሬ ከአንተ ጋራ ወደሚያደርገውና በመሐላ ወደሚያጸናው ኪዳን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ጋራ ትገባ ዘንድ፣

13 ለአንተ በሰጠው ተስፋና ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ በማለላቸው መሠረት እርሱ አምላክህ ይሆን ዘንድ፣ አንተም ሕዝቡ መሆንህን በዛሬው ዕለት ለማረጋገጥ ነው።

14 እኔም ይህን የመሐላ ኪዳን የማደርገው ከእናንተ ጋራ ብቻ አይደለም፤

15 ዐብራችሁን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እዚህ ከቆማችሁት ጋራ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ እዚህ ከሌሉትም ጋራ ነው።

16 በግብጽ ምድር እንዴት እንደ ኖርንና ወደዚህ ስንመጣም በየአገሮቹ ውስጥ እንዴት እንዳለፍን ራሳችሁ ታውቃላችሁ።

17 በመካከላቸውም አስጸያፊ ምስሎቻቸውንና የዕንጨትና የድንጋይ፣ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን አይታችኋል።

18 የእነዚህን ሕዝቦች አማልክት ለማምለክ ልቡን ከአምላካችን ከእግዚአብሔር የሚመልስ ወንድም ሆነ ሴት ጐሣም ሆነ ነገድ ዛሬ ከመካከላችሁ አለመገኘቱን አረጋግጡ፤ ከመካከልህ እንዲህ ያለውን መራራ መርዝ የሚያወጣ ሥር እንዳይኖር ተጠንቀቁ።

19 እንዲህ ያለው ሰው የዚህን መሐላ ቃል በሚሰማበት ጊዜ፣ በልቡ ራሱን በመባረክ፣ “እንደ ልቤ ሐሳብ ብኖርም እንኳ ሰላም አለኝ” ብሎ ያስባል። ይህም በለምለሙም ሆነ በደረቁ መሬት ላይ ጥፋትን ያመጣል።

20 እግዚአብሔር ለዚያ ሰው ፈጽሞ ይቅርታ አያደርግለትም፤ ቍጣውና ቅናቱ በርሱ ላይ ይነድድበታል። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ርግማን ሁሉ ይወርድበታል፤ እግዚአብሔርም ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል።

21 በዚህ የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው የኪዳኑ ርግማን መሠረት፣ እግዚአብሔር እርሱን ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል።

22 የሚቀጥለው ትውልድ ከእናንተ በኋላ የሚተኩት ልጆቻችሁና ከሩቅ አገር የሚመጡ እንግዶች በምድሪቱ የደረሰውን ታላቅ መቅሠፍትና እግዚአብሔር ያመጣባቸውን በሽታዎች ያያሉ።

23 ምድሪቱ በሙሉ የተቃጠለ ጨውና ዲን ዐመድ ትሆናለች። አንዳች ነገር አይተከልባትም፤ ምንም ነገር አያቈጠቍጥባትም፤ የሚያድግ ተክል አይገኝባትም። የሚደርስባት ውድመት እግዚአብሔር በታላቅ ቍጣ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ፣ እንደ አዳማና ስቦይ ጥፋት ይሆናል።

24 አሕዛብም ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በዚህች ምድር ላይ ይህን ለምን አደረገባት? ይህ አስፈሪና የሚነድድ ቍጣስ ለምን መጣባት?” ብለው ይጠይቃሉ።

25 መልሱም፣ “የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ፣ ከእነርሱ ጋራ የገባውን ኪዳን ሕዝቡ ስለ ተዉ ነው።

26 ወጥተውም የማያውቋቸውን፣ እርሱም ያላዘዛቸውን ሌሎችን አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም።

27 ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ርግማን ሁሉ እስኪያመጣባት ድረስ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በዚህች ምድር ላይ ነደደ።

28 በአስፈሪ ቍጣና በታላቅ መዓት እግዚአብሔር ከምድራቸው ነቀላቸው፤ አሁን እንደ ሆነውም ወደ ሌላ ምድር ጣላቸው” የሚል ይሆናል።

29 ምስጢር የሆነው ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ እንከተል ዘንድ ለዘላለም የእኛና የልጆቻችን ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告