ዘዳግም 28 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበመታዘዝ የሚገኝ በረከት 1 ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትከተል፣ አምላክህ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ያደርግሃል። 2 አምላክህን እግዚአብሔርን ብትታዘዝ፣ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ያንተ ይሆናሉ፤ አይለዩህምም። 3 በከተማ ትባረካለህ፣ በዕርሻህም ትባረካለህ። 4 የማሕፀንህ ፍሬ፣ የምድርህ አዝመራ፣ የእንስሳትህ ግልገሎች፣ የከብትህ ጥጃ፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህም ይባረካሉ። 5 እንቅብህና ቡሖ ዕቃህ ይባረካሉ። 6 ስትገባ ትባረካለህ፤ ስትወጣም ትባረካለህ። 7 እግዚአብሔር በአንተ ላይ የሚነሡ ጠላቶችህን በፊትህ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ በሰባት አቅጣጫም ከአንተ ይሸሻሉ። 8 እግዚአብሔር በጐተራህና እጅህ በነካው ሁሉ በረከቱን ይልካል። አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ላይ ይባርክሃል። 9 የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የምትጠብቅና በመንገዱ የምትሄድ ከሆነ፣ በመሐላ በሰጠህ ተስፋ መሠረት የተቀደሰ ሕዝቡ አድርጎ ያቆምሃል፤ 10 ከዚያም የምድር አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም። 11 እግዚአብሔርም ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በማሕፀንህ ፍሬ፣ በእንስሳትህም ግልገል፣ በምድርህም ሰብል የተትረፈረፈ ብልጽግና ይሰጥሃል። 12 እግዚአብሔር ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ለመስጠትና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ፣ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከአንዳቸውም አትበደርም። 13 እግዚአብሔርም ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በጥንቃቄ ብትጠብቅ፣ መቼውንም ቢሆን በላይ እንጂ ፈጽሞ በታች አትሆንም። 14 ሌሎችን አማልክት በመከተል እነርሱን በማገልገል ዛሬ ከምሰጥህ ትእዛዞች ቀኝም ግራም አትበል። አለመታዘዝ የሚያስከትላቸው ርግማኖች 15 ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ባትታዘዝ በዛሬዋ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ሁሉ በጥንቃቄ ባትከተላቸው፣ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ ይደርሱብሃል፤ ያጥለቀልቁሃልም፦ 16 በከተማ ትረገማለህ፤ በዕርሻም ትረገማለህ። 17 እንቅብህና ቡሖ ዕቃህ የተረገሙ ይሆናሉ። 18 የማሕፀንህ ፍሬ፣ የዕርሻህ ሰብል፣ የመንጋህ ጥጆች፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህ ይረገማሉ። 19 ስትገባ ትረገማለህ፤ ስትወጣም ትረገማለህ። 20 እርሱን በመተው ክፉ ድርጊት ከመፈጸምህ የተነሣ፣ እስክትደመሰስ ፈጥነህም እስክትጠፋ ድረስ እጅህ በነካው ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ርግማንን፣ መደናገርንና ተግሣጽን ይሰድድብሃል። 21 እግዚአብሔር ልትወርሳት ከምትገባባት ምድር ላይ እስኪያጠፋህ ድረስ በደዌ ይቀሥፍሃል። 22 እግዚአብሔር እስክትጠፋ ድረስ በሚቀሥፍ ደዌ፣ ትኵሳትና ዕባጭ፣ ኀይለኛ ሙቀትና ድርቅ፣ ዋግና አረማሞ ይመታሃል። 23 ከራስህ በላይ ያለው ሰማይ ናስ፣ ከእግርህ በታች ያለው ምድርም ብረት ይሆናል። 24 እግዚአብሔር የምድርህን ዝናብ ወደ ዐቧራነትና ወደ ትቢያነት ይለውጠዋል፤ ይህም እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል። 25 እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት እንድትሸነፍ ያደርግሃል፤ በአንድ አቅጣጫ ትመጣባቸዋለህ፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫ ከፊታቸው ትሸሻለህ፤ ለምድር መንግሥታትም ሁሉ መሸማቀቂያ ትሆናለህ። 26 ሬሳህ የሰማይ አሞሮችና የምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ በማስፈራራትም የሚያባርራቸው አይኖርም። 27 እግዚአብሔር በማትድንበት በግብጽ ብጉንጅ፣ በዕባጭ፣ በሚመግል ቍስልና በዕከክ ያሠቃይሃል። 28 እግዚአብሔር በእብደት፣ በዕውርነትና ግራ በማጋባት ያስጨንቅሃል። 29 በእኩለ ቀን፣ በጨለማ እንዳለ ዕውር በዳበሳ ትሄዳለህ። የምታደርገው ሁሉ አይሳካልህም። በየዕለቱ ትጨቈናለህ፤ ትመዘበራለህም፤ የሚታደግህ አይኖርም። 30 ሚስት ለማግባት ልጃገረድ ታጫለህ፤ ሌላው ግን ወስዶ ይደፍራታል። ቤት ትሠራለህ፣ ግን አትኖርበትም። ወይን ትተክላለህ፤ ፍሬውን ግን አትበላም። 31 በሬህ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ ከሥጋውም አንዳች አትቀምስም። አህያህም በግድ ይወሰድብሃል፤ አይመለስልህም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚያስጥላቸውም አይኖርም። 32 ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለባዕድ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ እጅህንም ለማንሣት ዐቅም ታጣለህ፤ ከዛሬ ነገ ይመጣሉ በማለትም ዐይኖችህ ሁልጊዜ እነርሱን በመጠባበቅ ይደክማሉ። 33 የምድርህንና የድካምህን ፍሬ ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ ዕድሜ ልክህን በጭካኔና በጭቈና ከመኖር በቀር የሚተርፍህ ነገር አይኖርም። 34 የምታየው ሁሉ ያሳብድሃል። 35 እግዚአብሔር ከእግርህ ጥፍር እስከ ራስህ ጠጕር በሚዛመት፣ ሊድን በማይችልና በሚያሠቃይ ቍስል ጕልበትህንና እግርህን ይመታሃል። 36 እግዚአብሔር አንተንና በላይህ ያነገሥኸውን ንጉሥ፣ አንተና አባቶችህ ወደማታውቁት ሕዝብ ይወስዳችኋል፤ ከዚያም ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። 37 እግዚአብሔር እንድትገባ በሚያደርግበት ምድር ለአሕዛብ ሁሉ መሸማቀቂያ፣ ማላገጫና መዘባበቻ ትሆናለህ። 38 በዕርሻ ላይ ብዙ ዘር ትዘራለህ፤ አንበጣ ስለሚበላው ግን፣ የምትሰበስበው ጥቂት ይሆናል። 39 ወይን ትተክላለህ፤ ትንከባከበዋለህ፤ ነገር ግን ትል ይበላዋልና ዘለላውን አትሰበስብም። 40 በአገርህ ምድር ሁሉ የወይራ ዛፍ ይኖርሃል፤ ፍሬው ስለሚረግፍብህ ግን፣ ዘይቱን አትጠቀምበትም። 41 ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትወልዳለህ፤ ነገር ግን በምርኮ ስለሚወሰዱ፣ ዐብረውህ አይኖሩም። 42 ዛፍህንና የምድርህን ሰብል ሁሉ የአንበጣ መንጋ ይወርረዋል። 43 በመካከልህ የሚኖር መጻተኛ ከአንተ በላይ ከፍ ከፍ ሲል፣ አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ። 44 እርሱ ያበድርሃል እንጂ አንተ አታበድረውም። እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተ ግን ጅራት ትሆናለህ። 45 እነዚህ ርግማኖች ሁሉ በአንተ ላይ ይመጣሉ፤ አምላክህን እግዚአብሔርን ስላልታዘዝህና የሰጠህን ትእዛዝና ሥርዐት ስላልጠበቅህ እስክትጠፋ ድረስ ይከተሉሃል፤ ይወርዱብሃልም። 46 ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም ምልክትና መገረም ይሆናሉ። 47 በብልጽግና ጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን በደስታና በሐሤት ስላላገለገልኸው፣ 48 በራብና በጥም፣ በእርዛትና በከፋ ድኽነት እግዚአብሔር የሚያስነሣብህን ጠላቶችህን ታገለግላለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በዐንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭንብሃል። 49 እግዚአብሔር እንደ ንስር ፈጥኖ የሚወርድንና ቋንቋውን የማታውቀውን ሕዝብ እጅግ ሩቅ ከሆነ፣ ከምድርም ዳርቻ ያስነሣብሃል፤ 50 ሽማግሌ የማያከብር፣ ለብላቴና የማይራራ፣ ሲያዩት የሚያስፈራ ሕዝብ ነው። 51 እስክትጠፋም ድረስ የእንስሳትህን ግልገልና የምድርህን ሰብል ይበላል፤ እስኪያጠፋህም ድረስ እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅ ሆነ ዘይት፣ የመንጋህን ጥጃ ሆነ የበግና የፍየል መንጋህን ግልገል አያስቀርልህም። 52 የምትታመንባቸውን ታላላቅ የተመሸጉ ቅጥሮች እስኪወድቁ ድረስ በመላው አገርህ ያሉትን ከተሞችህን ሁሉ ይከብባል፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ያሉትን ከተሞች በሙሉ ይወርራቸዋል። 53 ጠላቶችህ ከብበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ ከሥቃይ የተነሣ፣ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን፣ የወገብህ ፍሬ የሆኑትን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ። 54 ሌላው ይቅርና በመካከልህ በጣም ደግና ርኅሩኅ የሆነው ሰው እንኳ ለገዛ ወንድሙ ወይም ለሚወድዳት ሚስቱ ወይም ለተረፉት ልጆቹ አይራራላቸውም። 55 ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ላይም ቅንጣት ታኽል እንኳ ከእነርሱ ለአንዱ አያቀምስም፤ ከተሞችህ ሁሉ በመከበባቸው ጠላቶችህ ከሚያደርሱብህ ሥቃይ የተነሣ ለርሱ የቀረለት ይህ ብቻ ነውና። 56 በመካከልህ ተለሳልሳና ተቀማጥላ የምትኖር፣ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ፣ እግሯን ዐፈር ነክቶት የማያውቅ ሴት፣ የምትወድደውን ባሏን፣ የገዛ ወንድ ወይም ሴት ልጆቿን ትንቃለች። 57 ከማሕፀኗ የወጣውን እንግዴ ልጇንና የምትወልዳቸውን ሕፃናት ትጠየፋለች፤ ይህን የምታደርገውም በመከራው ወቅት ጠላቶችህ ከተሞችህን ከብበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ እነርሱን ደብቃ ለመብላት ስትል ነው። 58 በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የዚህን ሕግ ቃሎች በጥንቃቄ ባትከተልና አስደናቂና አስፈሪ የሆነውን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ስም ባታከብር፣ 59 እግዚአብሔር አስፈሪ መቅሠፍት፣ አስጨናቂና ለብዙ ጊዜ የሚቈይ መዓት፣ አሠቃቂና በቀላሉ የማይወገድ ደዌ በአንተና በዘሮችህ ላይ ይልክባችኋል። 60 የምትፈራቸውንም የግብጽ በሽታዎች ሁሉ ያመጣብሃል፤ በአንተም ላይ ይጣበቃሉ። 61 ደግሞም እግዚአብሔር በዚህ የሕግ መጽሐፍ ያልተጻፈውን ማንኛውንም ዐይነት ደዌና መከራ እስክትጠፋ ድረስ ያመጣብሃል። 62 ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዛችሁ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችሁ የነበራችሁት እናንተ ጥቂት ብቻ ትቀራላችሁ። 63 እግዚአብሔር እናንተን በማበልጸግና ቍጥራችሁን በማብዛት ደስ እንደ ተሠኘ፣ እናንተን በማጥፋትና በመደምሰስም ደስ ይለዋል፤ ልትወርሷት ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ። 64 ከዚያም እግዚአብሔር ከአንዱ የምድር ዳርቻ እስከ ሌላው ዳርቻ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይበትንሃል። በዚያ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቋቸውን ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። 65 በእነዚያ ሕዝቦች መካከል ዕረፍት አታገኝም፤ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ ቦታ አይኖርም። እዚያም እግዚአብሔር የሚጨነቅ አእምሮ፣ በናፍቆት የሚደክም ዐይንና ተስፋ የሚቈርጥ ልብ ይሰጥሃል። 66 ቀንም ሆነ ሌሊት በፍርሀት እንደ ተዋጥህ፣ ሕይወትህ ዋስትና ሳታገኝ፣ ዘወትር በሥጋት ትኖራለህ። 67 ልብህ በፍርሀት ከመሞላቱና ዐይንህ ከሚያየው የተነሣ፣ ሲነጋ፣ “ምነው አሁን በመሸ!” ሲመሽ ደግሞ፣ “ምነው አሁን በነጋ!” ትላለህ። 68 ዳግመኛ አትመለስባትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብጽ ይመልስሃል። እዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሮች እንድትሆኗቸው ለጠላቶቻችሁ ለመሸጥ ራሳችሁን ታቀርባላችሁ፤ የሚገዛችሁ ግን አይኖርም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.