ዘዳግም 27 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበጌባል ተራራ ላይ የቆመ መሠዊያ 1 ሙሴና የእስራኤል አለቆች ሕዝቡን እንዲህ ብለው አዘዙ፤ “ዛሬ የማዝዛችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤ 2 አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ ጥቂት ትልልቅ ድንጋዮችን አቁምና በኖራ ቅባቸው። 3 የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን ስትሻገር፣ የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ ጻፍባቸው። 4 ዮርዳኖስን እንደ ተሻገርህም፣ ዛሬ ባዘዝሁህ መሠረት እነዚህን ድንጋዮች በጌባል ተራራ ላይ ትከላቸው፤ በኖራም ቅባቸው። 5 እዚያም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የድንጋይ መሠዊያ ሥራ፤ በድንጋዮቹም ላይ ማንኛውንም የብረት መሣሪያ አታሳርፍባቸው። 6 የአምላክህን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ካልተጠረበ ድንጋይ ሥራ፤ በላዩም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርብበት። 7 በዚያም የኅብረት መሥዋዕት ሠዋ፤ ብላም፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ። 8 በድንጋዮቹ ላይ የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ ግልጽ አድርገህ ጻፍባቸው።” በጌባል ተራራ ላይ የተነገረ መርገም 9 ሙሴና ሌዋውያን ካህናትም ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ አሉ፤ “እስራኤል ሆይ፤ ጸጥ ብለህ ስማ! አንተ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል፤ 10 አምላክህን እግዚአብሔርን ታዘዝ፤ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ጠብቅ።” 11 ሙሴ በዚያ ዕለት ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዘ፦ 12 ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዮሴፍና ብንያም ሕዝቡን ለመባረክ በገሪዛን ተራራ ላይ ይቁሙ። 13 ሮቤል፣ ጋድ፣ አሴር፣ ዛብሎን፣ ዳንና ንፍታሌምም በጌባል ተራራ ላይ ለመርገም ይቁሙ። 14 ሌዋውያን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገሩ፦ 15 “የእጅ ጥበብ ባለሙያ የሠራውን፣ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ የሆነውን ምስል የሚቀርጽ ወይም ጣዖትን የሚያበጅ፣ በስውርም የሚያቆም ሰው የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 16 “አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 17 “የባልንጀራውን የድንበር ድንጋይ ከቦታው የሚያንቀሳቅስ የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 18 “ዐይነ ስውሩን በተሳሳተ መንገድ የሚመራ፣ የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 19 “በመጻተኛው፣ አባት በሌለውና በመበለቲቱ ላይ ፍትሕ የሚያዛባ የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 20 “ከአባቱ ሚስት ጋራ የሚተኛ የተረገመ ይሁን፤ የአባቱን መኝታ ያረክሳልና።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 21 “ከማናቸውም እንስሳ ጋራ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚያደርግ የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 22 “የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ ከሆነችው እኅቱ ጋራ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽም የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 23 “ከዐማቱ ጋራ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽም የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 24 “በድብቅ ባልንጀራውን የሚገድል የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 25 “ንጹሕን ሰው ለመግደል ጕቦ የሚቀበል የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። 26 “የዚህን ሕግ ቃሎች በመፈጸም የማይጸና የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.