Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘዳግም 26 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ዐሥራትና በኵራት

1 አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ምድር ስትገባ፣ ስትወርሳትና ስትኖርባት፣

2 አምላክህ እግዚአብሔር ከሚሰጥህ ምድር ከምትሰበስበው ሰብል ሁሉ፣ በኵራት ወስደህ በቅርጫት ውስጥ አድርገው፤ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ፤

3 በዚያም ወቅት ለሚያገለግለው ካህን፣ “እግዚአብሔር ለእኛ ሊሰጠን ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር እንደ ገባሁ ዛሬ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እናገራለሁ” በለው።

4 ካህኑም ቅርጫቱን ከእጅህ ተቀብሎ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ለፊት ያስቀምጠዋል።

5 አንተም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፤ “አባቴ ዘላን ሶርያዊ ነበር፤ ከጥቂት ሰዎችም ጋራ ወደ ግብጽ ወረደ፤ በዚያም ተቀመጠ፤ ታላቅ፣ ኀያልና ቍጥሩ የበዛ ሕዝብ ሆነ።

6 ግብጻውያን ግን ከባድ ሥራ በማሠራት አንገላቱን፤ አሠቃዩንም።

7 ከዚያ በኋላ የአባቶቻችን አምላክ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፤ እግዚአብሔርም ጩኸታችንን ሰማ፤ ጕስቍልናችንን፣ ድካማችንንና የተፈጸመብንን ግፍ ተመለከተ።

8 ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፣ በታላቅ ድንጋጤ፣ በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ከግብጽ አወጣን።

9 ወደዚህ ስፍራ አመጣን፤ ማርና ወተት የምታፈስሰውን ይህችን ምድር ሰጠን፤

10 አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ እነሆ፤ አንተ የሰጠኸኝን የምድሪቱን በኵራት አምጥቻለሁ።” ቅርጫቱንም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አስቀምጠው፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ስገድ።

11 ከዚያም አንተ፣ ሌዋዊውና በመካከልህ የሚኖረው መጻተኛ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለቤትህ በሰጠው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ይበላችሁ።

12 የዐሥራት ዓመት የሆነውን የሦስተኛውን ዓመት ምርት አንድ ዐሥረኛ ለይተህ ካወጣህ በኋላ በየከተሞችህ ውስጥ በልተው እንዲጠግቡ፣ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ስጣቸው፤

13 ከዚያ በኋላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲህ በል፤ “በሰጠኸኝ ትእዛዝ መሠረት የተቀደሰውን ክፍል ከቤቴ አውጥቼ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ሰጥቻለሁ። ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ አንዱንም አልረሳሁም።

14 በሐዘን ላይ ሳለሁ፣ ከተቀደሰው ክፍል ላይ ምንም አልበላሁም፤ ባልነጻሁበትም ጊዜ ከዚሁ ላይ ያነሣሁትም ሆነ ለሙታን ያቀረብሁት ምንም ነገር የለም፤ አምላኬን እግዚአብሔርን ታዝዣለሁ፤ ያዘዝኸኝንም ሁሉ ፈጽሜአለሁ።

15 ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ተመልከት፤ ሕዝብህን እስራኤልንና ለአባቶቻችን በመሐላ ቃል በገባኸው መሠረት፣ ለእኛ የሰጠኸንን ይህችን ማርና ወተት የምታፈስሰውን ምድር ባርክ።”


የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ስለ መጠበቅ

16 አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ሥርዐትና ሕግ ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ ያዝዝሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህ፣ በፍጹምም ነፍስህ ትፈጽመው ዘንድ ተጠንቀቅ።

17 እግዚአብሔር አምላክህ እንደ ሆነ በመንገዱም እንደምትሄድ፣ ሥርዐቱን፣ ትእዛዙንና ሕጉን እንደምትጠብቅና እንደምትታዘዝለት በዛሬዪቱ ዕለት ተናግረሃል።

18 እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት አንተ፣ ሕዝቡና ርስቱ መሆንህን፣ ትእዛዙንም ሁሉ እንደምትጠብቅ በዛሬው ዕለት ተናግሯል።

19 ከፈጠራቸው ሕዝቦች ሁሉ በላይ በምስጋና፣ በስም፣ በክብርም ከፍ እንደሚያደርግህና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ እንደምትሆን ተናግሯል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告