ዘዳግም 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምገዳዩ ላልታወቀ ሰው ስለሚቀርብ ማስተስረያ 1 አምላክህ እግዚአብሔር እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር አንድ ሰው ተገድሎ ሜዳ ላይ ቢገኝና ገዳዩም ማን እንደ ሆነ ባይታወቅ፣ 2 ሽማግሌዎችህና ዳኞችህ ወጥተው ሬሳው ወድቆ ከተገኘበት ስፍራ አንሥቶ በአቅራቢያው እስካሉት ከተሞች ድረስ ያለውን ርቀት ይለኩ። 3 ከዚያም ሬሳው ወድቆ ከተገኘበት ስፍራ በጣም ቅርብ የሆነችው ከተማ ሽማግሌዎች ለሥራ ያልደረሰችና ቀንበር ያልተጫነባትን ጊደር ይዘው፣ 4 ከዚያ በፊት ታርሶ ወይም ተዘርቶበት ወደማይታወቅ ወራጅ ውሃ ወዳለበት ሸለቆ ያምጡት። በዚያ ሸለቆም የጊደሪቱን ዐንገት ይስበሩ፤ 5 እንዲያገለግሉና በእግዚአብሔር ስም እንዲባርኩ፣ በማንኛውም የክርክርና የጥቃት ጕዳዮች ሁሉ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ፣ አምላክህ እግዚአብሔር መርጧቸዋልና የሌዊ ልጆች ካህናቱ ወደ ፊት ይቅረቡ። 6 ከዚያም ሬሳው በተገኘበት አቅራቢያ ባለችው ከተማ የሚኖሩ ሽማግሌዎች ሁሉ፣ በሸለቆው ውስጥ፣ ዐንገቷ በተሰበረው ጊደር ላይ እጃቸውን ይታጠቡ። 7 እንዲህም ብለው ይናገሩ፤ “እጆቻችን ደም አላፈሰሱም፤ ድርጊቱ ሲፈጸምም ዐይኖቻችን አላዩም። 8 እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ተቤዠኸው ሕዝብህ ስለ እስራኤል ብለህ ይህን ስርየት ተቀበል፤ ሕዝብህንም በፈሰሰው ንጹሕ ደም በደለኛ አታድርግ።” ስለ ፈሰሰውም ደም ስርየት ይደረግላቸዋል። 9 አንተም በእግዚአብሔር ፊት ቀና የሆነውን ስታደርግ፣ የንጹሑን ደም የማፍሰስ በደልን ከመካከልህ ታስወግዳለህ። የተማረከች ሴት ስለ ማግባት 10 ከጠላቶችህ ጋራ ጦርነት ልትገጥም ወጥተህ አምላክህ እግዚአብሔር እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶህ በማረክህ ጊዜ፣ 11 ከምርኮኞቹ መካከል መልከ መልካም ሴት አይተህ ብትማርክህ፣ ሚስትህ ልታደርጋት ትችላለህ። 12 ወደ ቤትህ ውሰዳት፤ ጠጕሯን ትላጭ፤ ጥፍሯንም ትቍረጥ። 13 ስትማረክ የለበሰችውንም ልብስ ታውልቅ፤ እቤትህ ተቀምጣ ለአባትና ለእናቷ ወር ሙሉ ካለቀሰችላቸው በኋላ፣ ልትደርስባትና ባል ልትሆናት፣ እርሷም ሚስት ልትሆንህ ትችላለች። 14 በርሷ ደስተኛ ባትሆን፣ ወደምትፈልገው እንድትሄድ ነጻነት ስጣት፤ ውርደት ላይ ጥለሃታልና ልትሸጣት ወይም እንደ ባሪያ ልትቈጥራት አይገባህም። የበኵር ልጅ መብት 15 አንድ ሰው ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፣ አንደኛዋን የሚወድዳት፣ ሌላዋን ግን የሚጠላት ቢሆን፣ ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ወልደውለት በኵር ልጁ ግን የተወለደው ከማይወድዳት ሚስቱ ቢሆን፣ 16 ንብረቱን ለልጆቹ በሚያወርስበት ጊዜ፣ የብኵርናን መብት ከማይወድዳት ሚስቱ ከወለደው በኵር ልጅ ገፎ፣ ከሚወድዳት ሚስቱ ለተወለደው ልጁ በአድልዎ መስጠት አይገባውም፤ 17 ይልቁንም ከተጠላችው ሚስቱ ለተወለደው ልጅ ካለው ሀብት ሁሉ ሁለት እጅ ድርሻውን በመስጠት ብኵርናውን ያስታውቅ፤ ያ ልጅ የአባቱ ኀይል መጀመሪያ ነውና፣ የብኵርና መብት የራሱ ነው። የማይታዘዝ ልጅ 18 አንድ ሰው፣ የአባቱን ወይም የእናቱን ትእዛዝ የማይሰማ፣ ቢቀጡትም የማይታረም እልከኛና ዐመፀኛ ልጅ ቢኖረው፣ 19 አባትና እናቱ ይዘው በሚኖሩበት ከተማ በር ወዳሉት አለቆች ያምጡት፤ 20 “ይህ ልጃችን እልከኛና ዐመፀኛ ነው፤ አይታዘዘንም፤ አባካኝና ሰካራም ነው” ብለው ለከተማው አለቆች ይንገሯቸው። 21 ከዚያም በኋላ የከተማዪቱ ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፤ ክፉውንም ከመካከልህ አስወግድ፤ እስራኤልም ሁሉ ይህን ሰምቶ ይፈራል። ልዩ ልዩ ሕጎች 22 አንድ ሰው ለሞት የሚያበቃ በደል ፈጽሞ ቢገደልና በድኑ በዕንጨት ላይ ቢሰቀል፣ 23 በድኑን በዕንጨት ላይ እንደ ተሰቀለ አታሳድረው፤ ምክንያቱም በዕንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና፤ አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሚሰጥህን ምድር እንዳታረክስ፣ በዚያ ዕለት ቅበረው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.