ዘዳግም 20 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምለጦርነት መውጣት 1 ጠላቶችህን ለመውጋት ወደ ጦርነት ስትሄድ፣ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ከአንተ የሚበልጥ ሰራዊትንም በምታይበት ጊዜ አትፍራቸው፤ ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነውና። 2 ወደ ውጊያው ቦታ ስትቃረቡ፣ ካህኑ ወደ ፊት ወጣ ብሎ ለሰራዊቱ ይናገር፤ 3 እንዲህም ይበል፤ “እስራኤል ሆይ ስማ፤ በዛሬው ቀን ጠላቶቻችሁን ለመግጠም ወደ ጦርነት ልትገቡ ነው፤ ልባችሁ አይባባ፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በጠላቶቻችሁ ፊት አትሸበሩ፤ 4 ድልን ያቀዳጃችሁ ዘንድ ስለ እናንተ ጠላቶቻችሁን ሊወጋ ዐብሯችሁ የሚወጣው አምላካችሁ እግዚአብሔር ነውና።” 5 አለቆቹም ለሰራዊቱ እንዲህ ይበሉ፤ “አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ አለን? ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ፤ አለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ቤቱን የሚያስመርቀው ሌላ ሰው ይሆናል። 6 ወይን ተክሎ ገና ያልበላለት አለን? ወደ ቤቱ ይመለስ፤ አለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ወይኑን ሌላ ሰው ይበላዋል። 7 ሚስት አጭቶ ያላገባት አለን? ወደ ቤቱ ይመለስ፤ አለዚያ በጦርነቱ ይሞትና ሌላ ሰው ያገባታል።” 8 ከዚያም አለቆቹ፣ “የሚፈራ ወይም ልቡ የሚባባ ሰው አለን? የወንድሞቹም ልብ እንዳይባባ ወደ ቤቱ ይመለስ” በማለት ጨምረው ይናገሩ። 9 አለቆቹ ለሰራዊቱ ተናግረው ሲያበቁ፣ አዛዦችን በሰራዊቱ ላይ ይሹሙ። 10 አንድን ከተማ ለመውጋት በምትዘምትበት ጊዜ፣ አስቀድመህ ለሕዝቧ የሰላም ጥሪ አስተላልፍ፤ 11 ከተቀበሉህና ደጃቸውን ከከፈቱልህ፣ በከተማዪቱ ውስጥ ሕዝብ ሁሉ ገባርህ ይሁን፤ ያገልግልህም። 12 ዕርቀ ሰላምን ባለመቀበል ውጊያን ከመረጡ፣ ከተማዪቱን ክበባት። 13 አምላክህ እግዚአብሔር አሳልፎ በእጅህ በሰጠህ ጊዜ፣ በውስጧ ያሉትን ወንዶች በሙሉ በሰይፍ ግደላቸው። 14 ነገር ግን ሴቶቹን ሕፃናትን፣ እንስሳቱንና በከተማዪቱ ውስጥ የሚገኘውን ማንኛውንም ነገር በምርኮ ለራስህ አድርግ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከጠላቶችህ የሚሰጥህን ምርኮ ልትጠቀምበት ትችላለህ። 15 እንግዲህ የአካባቢህ አሕዛብ ከተሞች ባልሆኑትና ከአንተ እጅግ ርቀው በሚገኙት ከተሞች ሁሉ ላይ የምታደርገው ይኸው ነው። 16 አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ በአሕዛብ ከተሞች ውስጥ፣ እስትንፋስ ያለውን ነገር አታስተርፍ። 17 ኬጢያዊውን፣ አሞራዊውን፣ ከነዓናዊውን፣ ፌርዛዊውን፣ ኤዊያዊውንና ኢያቡሳዊውን አምላክህ እግዚአብሔር ባዘዘህ መሠረት ፈጽመህ ደምስሳቸው፤ 18 አለዚያ አማልክታቸውን በሚያመልኩበት ጊዜ የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ተግባራት ሁሉ ታደርግ ዘንድ ያስተምሩሃል፤ በአምላክህ በእግዚአብሔርም ላይ ኀጢአት ትሠራለህ። 19 አንድን ከተማ ተዋግተህ ለመያዝ የረጅም ጊዜ ከበባ ካደረግህ፣ ዛፎቹን በመጥረቢያ ጨፍጭፈህ አታጥፋ፤ የእነርሱን ፍሬ መብላት ትችላለህና አትቍረጣቸው፤ ከብበህ የምታጠፋቸው የሜዳ ዛፎች ሰዎች ናቸውን? 20 የሚበላ ፍሬ እንደማያፈራ የምታውቀውን ዛፍ ግን ልትቈርጠውና ጦርነት የምታካሂድባትን ከተማ በድል እስክትቈጣጠራት ድረስ ለከበባው ምሽግ መሥሪያ ልትጠቀምበት ትችላለህ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.