Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘዳግም 19 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መማጸኛ ከተሞች
19፥1-14 ተጓ ምብ – ዘኍ 35፥6-34 ፤ ዘዳ 4፥41-43 ፤ ኢያ 20፥1-9

1 አምላክህ እግዚአብሔር ምድራቸውን ለአንተ የሚሰጥባቸውን አሕዛብ በሚደመስሳቸው ጊዜና አንተም እነርሱን አስለቅቀህ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸው በምትቀመጥበት ጊዜ፣

2 አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር አማካይ ስፍራ፣ ሦስት ከተሞችን ለራስህ ለይ።

3 ሰው የገደለ ሁሉ እንዲሸሽባቸው አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር መንገዶችን ሠርተህ፣ በሦስት ክፈላቸው።

4 በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ገድሎ ሕይወቱን ለማትረፍ ለሚሸሽ ሰው መመሪያው የሚከተለው ነው።

5 እነሆ፤ አንድ ሰው ከባልንጀራው ጋራ ዕንጨት ለመቍረጥ ወደ ጫካ ቢሄድ፣ ዛፉን ለመጣል መጥረቢያውን በሚሰነዝርበት ጊዜ ብረቱ ከእጀታው ወልቆ ባልንጀራውን በመምታት ቢገድለው፣ ያ ሰው ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ ሕይወቱን ማትረፍ ይችላል።

6 አለዚያ በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ቢገድል፣ መንገዱ ረዥም ከሆነ ደም ተበቃዩ በንዴት ተከታትሎ ይደርስበትና መገደል የማይገባውን ሰው ሊገድል ይችላል።

7 ሦስት ከተሞችን ለራስህ እንድትለይ ያዘዝሁህ በዚሁ ምክንያት ነው።

8 ለአባቶችህ በመሐላ በገባላቸው ቃል መሠረት፣ አምላክህ እግዚአብሔር ወሰንህን ሲያሰፋውና ለእነርሱ በሰጣቸው መሠረት ምድሪቱን ሁሉ ሲሰጥህ፣

9 አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድድና ምን ጊዜም በመንገዱ እንድትሄድ ዛሬ የማዝዝህን እነዚህን ሕግጋት ሁሉ በጥንቃቄ የምትጠብቅ ከሆነ፣ በእነዚህ ላይ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትጨምራለህ።

10 አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር የንጹሕ ሰው ደም እንዳይፈስስና በሚፈስሰውም ደም በደለኛ እንዳትሆን ይህን አድርግ።

11 ይሁን እንጂ አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢጠላው፣ አድፍጦ ጥቃት ቢያደርስበት፣ ቢገድለውና ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፣

12 የሚኖርባት ከተማ ሽማግሌዎች ሰው ልከው ከከተማው ያስመጡት፤ እንዲገድለውም ለደም ተበቃዩ አሳልፈው ይስጡት።

13 አትራራለት፤ ነገር ግን መልካም እንዲሆንልህ የንጹሑን ደም በደል ከእስራኤል አስወግድ።

14 አምላክህ እግዚአብሔር እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ለአንተ በሚተላለፍልህ ርስት ላይ የቀድሞ ሰዎች ያስቀመጡትን የባልንጀራህን የድንበር ምልክት አታንሣ።


ምስክሮች

15 በማንኛውም ወንጀል ወይም ሕግ በመተላለፍ ሰውን ጥፋተኛ ለማድረግ፣ አንድ ምስክር አይበቃም፤ ነገር በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች የምስክር አፍ መረጋገጥ አለበት።

16 ተንኰለኛ የሆነ ምስክር አንድን ሰው በሐሰት ቢከስስ፣

17 ክርክሩ የሚመለከታቸው ሁለቱ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት፣ በዚያ ወቅት በሚያገለግሉት ካህናትና ፈራጆች ፊት ይቁሙ።

18 ፈራጆችም ጕዳዩን በጥልቅ ይመርምሩት፤ ያም ምስክር በወንድሙ ላይ በሐሰት የመሰከረ መሆኑ ከተረጋገጠ፣

19 በወንድሙ ላይ ለማድረግ ያሰበውን በርሱ ላይ አድርጉበት፤ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።

20 የቀሩትም ሰዎች ይህን ሰምተው ይፈራሉ፤ እንዲህ ያለው ክፉ ነገርም ለወደፊቱ በመካከልህ ከቶ አይደገምም።

21 ርኅራኄ አታድርግ፤ ሕይወት በሕይወት፣ ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ፣ እጅ በእጅ፣ እግር በእግር ይመለስ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告