Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘዳግም 18 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የካህናትና የሌዋውያን የመባ ድርሻ

1 ሌዋውያን ካህናት፣ የሌዊ ነገድም ሁሉ ከእስራኤል ጋራ የመሬት ድርሻ ወይም ርስት አይኖራቸውም፤ ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው መባ ይብሉ፤ ድርሻቸው ነውና።

2 በወንድሞቻቸው መካከል ርስት አይኖራቸውም፤ በሰጣቸው ተስፋ መሠረት እግዚአብሔር ርስታቸው ነው።

3 ኰርማ ወይም በግ የሚሠዋው ሕዝብ ለካህኑ የሚሰጠው ድርሻ ወርቹን፣ መንገጭላውንና ሆድ ዕቃውን ነው።

4 የእህልህን፣ የአዲሱን ወይንህንና የዘይትህን በኵራት እንዲሁም ከበጎችህ በመጀመሪያ የተሸለተውን ጠጕር ትሰጣለህ፤

5 በእግዚአብሔር ስም ቆሞ ለዘላለም ያገለግል ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ከነገዶችህ ሁሉ እርሱንና ዘሮቹን መርጧል።

6 አንድ ሌዋዊ ከሚኖርበት ከየትኛውም በእስራኤል ካሉት ከተሞችህ መካከል በፍጹም ፈቃድ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ስፍራ ቢመጣ፣

7 በእግዚአብሔር ፊት ቆመው እንደሚያገለግሉት ሌዋውያን ወንድሞቹ፣ እርሱም በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ያገልግል።

8 ከቤተ ሰቡ ንብረት ሽያጭ ላይ ገንዘብ ቢቀበል እንኳ፣ ባልንጀሮቹ ከሚያገኙት ጥቅም እኩል ይካፈላል።


አስጸያፊ ድርጊቶች

9 አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ፣ በዚያ የሚኖሩት አሕዛብ የሚፈጽሙትን አስጸያፊ መንገድ አትከተል።

10 በመካከልህ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ ሟርተኛ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ጠንቋይ

11 ወይም በድግምት የሚጠነቍል፣ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ።

12 እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነውና። ከእነዚህ አስጸያፊ ልምዶች የተነሣም አምላክህ እግዚአብሔር እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ያባርራቸዋል።

13 በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ነውር አልባ ሁን።


ነቢይ ስለ መነሣቱ

14 ምድራቸውን የምታስለቅቃቸው አሕዛብ፣ መተተኞችን ወይም ሟርተኞችን ያደምጣሉ፤ አንተ ግን ይህን እንድታደርግ አምላክህ እግዚአብሔር አልፈቀደልህም።

15 አምላክህ እግዚአብሔር እንደ እኔ ያለ ነቢይ ከወንድሞቻችሁ መካከል ያስነሣልሃል፤ እርሱን ስማ።

16 በኮሬብ ጉባኤ በተደረገበት ዕለት፣ “እንዳልሞት የአምላክህ የእግዚአብሔርን ድምፅ አልስማ፤ እንዲህ ያለውንም አስፈሪ እሳት ደግሜ አልይ” ብለህ አምላክህን እግዚአብሔርን የጠየቅኸው ይህን ነውና።

17 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የተናገሩት መልካም ነው፤

18 ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌን በአፉ አደርጋለሁ፤ የማዝዘውንም ሁሉ ይነግራቸዋል።

19 ማንም ሰው ነቢዩ በስሜ የሚናገረውን ቃሌን ባይሰማ፣ እኔ ራሴ በተጠያቂነት እይዘዋለሁ።

20 ነገር ግን እንዲናገር እኔ ያላዘዝሁትን ቃል በድፍረት በስሜ የሚናገርም ሆነ በሌሎች አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ ይገደል።”

21 አንተም በልብህ፣ “እግዚአብሔር ያልተናገረውን መልእክት እንዴት ማወቅ እንችላለን?” ብትል፣

22 ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም የተናገረው ካልተፈጸመ ወይም እውነት ሆኖ ካልተገኘ፣ መልእክቱ እግዚአብሔር የተናገረው አይደለም። ያ ነቢይ በድፍረት ተናግሮታልና እርሱን አትፍራው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告