Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘዳግም 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 እንከን ወይም ጕድለት ያለበትን በሬ ወይም በግ በርሱ ዘንድ አስጸያፊ ነውና ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋ።

2 እግዚአብሔር በሚሰጥህ ከተሞች በአንዲቱ ዐብሮህ የሚኖር ወንድ ወይም ሴት ኪዳኑን በማፍረስ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ሲፈጽም ቢገኝ፣

3 ትእዛዜንም በመተላለፍ ባዕዳን አማልክትን ያመለከ፣ ለርሱም ማለትም ለፀሓይ ወይም ለጨረቃ ወይም ለሰማይ ከዋክብት የሰገደ፣

4 አንተም ይህ መደረጉን ብትሰማ፣ ነገሩን በጥንቃቄ መርምር፤ የተባለውም እውነት ከሆነና እንዲህ ያለው አስጸያፊ ነገር በእስራኤል ዘንድ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፣

5 ይህን ክፉ ድርጊት የፈጸመውን ወንድ ወይም ሴት ወደ ከተማ ደጅ ወስደህ፣ ያን ሰው እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው።

6 ሞት የሚገባው ሰው፣ በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ምስክርነት ይገደል፤ ነገር ግን በአንድ ሰው ምስክርነት ብቻ ማንም ሰው አይገደል።

7 ሲገደልም መጀመሪያ የምስክሮቹ እጅ፣ ቀጥሎም የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይረፍበት፤ ክፉን ከመካከልህ አስወግድ።


የፍርድ አደባባይ

8 በአንድ የነፍስ ግድያ ዐይነትና በሌላ፣ በአንድ ዐይነት ሕጋዊ ክርክርና በሌላ፣ ወይም በአንድ የክስ ዐይነትና በሌላ መካከል ውሳኔ የሚጠይቅ ማንኛውም ጕዳይ ቢነሣ፣ ከዐቅምህ በላይ የሆነ ጕዳይ በከተሞችህ ውስጥ ቢያጋጥምህ፣ ተነሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ስፍራ ውጣ፤

9 ካህናት ወደሆኑት ሌዋውያንና በዚያ ጊዜ ዳኛ ወደ ሆነው ሰው ሄደህ ስለ ጕዳዩ ጠይቃቸው፤ እነርሱም ውሳኔውን ይነግሩሃል።

10 አንተም እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ እነርሱ በሚሰጡህ ውሳኔ መሠረት ፈጽም። እንድትፈጽም የሚሰጡህን መመሪያ ሁሉ በጥንቃቄ አድርግ።

11 በሚያስተምሩህ ሕግና በሚሰጡህ መመሪያዎች መሠረት ፈጽም። እነርሱ ከሚነግሩህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።

12 አምላክህን እግዚአብሔርን ለማገልገል በዚያ የሚቆመውን ካህን ወይም ዳኛ የሚንቅ ይገደል፤ ከእስራኤልም መካከል ክፉውን አስወግድ።

13 ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲሰማ ይፈራል፤ ከዚያ ወዲያም እንዲህ ያለውን የንቀት ድርጊት አይደግመውም።


ንጉሥን ስለ ማንገሥ

14 አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ስትገባ፣ በምትወርሳትና በምትቀመጥባት ምድር፣ “በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ፣ እኔም በላዬ ንጉሥ ላንግሥ” ብትል፣

15 አምላክህ እግዚአብሔር የሚመርጠውን ንጉሥ በላይህ ታነግሣለህ፤ ከገዛ ወንድሞችህ መካከል እንጂ፣ እስራኤላዊ ወንድምህ ያልሆነውን ባዕድ በላይህ አታንግሥ።

16 ንጉሡም ብዙ ፈረሶችን ለራሱ አያብዛ፤ ወይም ደግሞ የፈረሰኞችን ቍጥር ለመጨመር ሕዝቡን ወደ ግብጽ አይመልስ፤ እግዚአብሔር፣ “በዚያ መንገድ ፈጽሞ አትመለሱ” ብሏችኋልና።

17 ልቡ እንዳይስትም ብዙ ሚስቶችን አያግባ፤ ብዙ ብርና ወርቅም አያግበስብስ።

18 በመንግሥቱ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበትም ጊዜ፣ የዚህን ሕግ ቅጅ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ በጥቅልል መጽሐፍ ለራሱ ይጻፍ።

19 አምላኩን እግዚአብሔርን ማክበር ይማር ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉና ይህን ሥርዐት በጥንቃቄ ይከተል ዘንድ ከርሱ ጋራ ይሁን፤ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ያንብበው።

20 እርሱና ዘሮቹ በእስራኤል ላይ ረዥም ዘመን ይገዙ ዘንድ፣ ከሕጉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አይበል፤ ራሱን ከሌሎች ወንድሞቹ በላይ የተሻለ አድርጎ አይቍጠር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告