ዘዳግም 16 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምፋሲካ 16፥1-8 ተጓ ምብ – ዘፀ 12፥14-20 ፤ ዘሌ 23፥4-8 ፤ ዘኍ 28፥16-25 1 አምላክህ እግዚአብሔር በአቢብ ወር ከግብጽ በሌሊት ስላወጣህ፣ የአቢብን ወር ጠብቅ፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፋሲካ አክብርበት። 2 እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ በሚመርጠው ስፍራ ከበግና ከፍየል ወይም ከመንጋህ አንዱን እንስሳ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ፋሲካ አድርገህ ሠዋው። 3 እርሾ ያለበት ቂጣ አትብላ፤ ከግብጽ የወጣኸው በችኰላ ነውና ከግብጽ የወጣህበትን ጊዜ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ታስብ ዘንድ እርሾ የሌለበት ቂጣ ሰባት ቀን ብላ። 4 በምድርህ ሁሉ ላይ በአንተ ዘንድ ለሰባት ቀን እርሾ አይገኝ፤ በመጀመሪያው ዕለት ምሽት ከምትሠዋውም ላይ ማንኛውንም ሥጋ ጧት ድረስ እንዲቈይ አታድርግ። 5 አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ በማናቸውም ከተማ ፋሲካን መሠዋት አይገባህም፤ 6 ነገር ግን ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ፣ ፀሓይ ስትጠልቅ ምሽቱ ላይ ከግብጽ በወጣህበት ሰዓት፣ በዚያ ፋሲካን ሠዋ። 7 ሥጋውንም ጠብሰህ አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ ብላ፤ ሲነጋም ወደ ድንኳንህ ተመልሰህ ሂድ። 8 ለስድስት ቀን እርሾ የሌለበት ቂጣ ብላ፤ በሰባተኛው ቀን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ጉባኤ አድርግ፤ ሥራም አትሥራበት። የመከር በዓል 16፥9-12 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥15-22 ፤ ዘኍ 28፥26-31 9 እህልህን ማጨድ ከምትጀምርበት ዕለት አንሥቶ ሰባት ሳምንት ቍጠር። 10 ከዚያም በኋላ አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ መጠን፣ የእጅህን የበጎ ፈቃድ ስጦታ በማቅረብ የሰባቱ ሱባዔ የመከር በዓል አምላክህን እግዚአብሔርን አክብር። 11 አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችህ፣ በከተሞችህ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ፣ በመካከልህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች አምላክህ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። 12 አንተም በግብጽ ባሪያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ይህንም በጥንቃቄ ጠብቅ። የዳስ በዓል 16፥13-17 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥33-43 ፤ ዘኍ 29፥12-39 13 የእህልህን ምርት ከዐውድማህ፣ ወይንህንም ከመጭመቂያህ ከሰበሰብህ በኋላ፣ የዳስን በዓል ሰባት ቀን አክብር። 14 በበዓልህ አንተ፣ ወንድና ሴት ልጅህ፣ ወንድና ሴት አገልጋይህ፣ በከተማው ያለ ሌዋዊ፣ መጻተኛ፣ አባት አልባውና መበለቲቱ ደስ ይበላችሁ። 15 እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በዓሉን ሰባት ቀን አክብር፤ አምላክህ እግዚአብሔር በእህል ምርትህና በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክሃል፤ ደስታህም ፍጹም ይሆናል። 16 ወንዶችህ ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ፣ በቂጣ በዓል፣ በሰባቱ ሱባዔ የመከር በዓልና በዳስ በዓል ላይ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይቅረቡ፤ ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ባዶ እጁን አይቅረብ። 17 አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ መጠን እያንዳንዱ ይስጥ። ስለ ፍርድ አሰጣጥ 18 አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ከተሞች ሁሉ ለየነገዶችህ ዳኞችንና አለቆችን ሹም፤ እነርሱም ሕዝቡን በጽድቅ ፍርድ ይዳኙ። 19 ፍርድ አታዛባ፤ አድልዎ አታድርግ፤ ጕቦ አትቀበል፤ ጕቦ የጠቢባንን ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። 20 በሕይወት እንድትኖርና አምላክህ እግዚአብሔር የሚሰጥህን ምድር እንድትወርስ፣ የጽድቅ ፍርድን ብቻ ተከተል። ሌሎችን አማልክት ስለ ማምለክ 21 ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በምትሠራው መሠዊያ አጠገብ የአሼራን ምስል የዕንጨት ዐምድ አታቁም። 22 አምላክህ እግዚአብሔር የሚጠላውን ማምለኪያ ዐምድ ለአንተ አታቁም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.