ዘዳግም 14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምንጹሕና ንጹሕ ያልሆነ ምግብ 14፥3-20 ተጓ ምብ – ዘሌ 11፥1-23 1 እናንተ የአምላካችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትቦጭቁ፤ ከግንባራችሁ በላይ ያለውን ጠጕር አትላጩ፤ 2 ምክንያቱም አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ ለራሱ የተለየ ሕዝብ እንድትሆንለት እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ አንተን መርጦሃል። 3 ማንኛውንም ርኩስ ነገር አትብላ። 4 የምትበሏቸው እንስሳት እነዚህ ናቸው፤ በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ 5 ዋላ፣ ድኵላ፣ ሰስ፣ የበረሓ ፍየል፣ ዋሊያ፣ ሚዳቋ፣ አጋዘን። 6 ሰኰናው ስንጥቅ የሆነውን፣ ለሁለት የተከፈለውንና የሚያመሰኳውን ማንኛውንም እንስሳ ብላ። 7 ነገር ግን ከሚያመሰኩት ወይም ሰኰናቸው ከተሰነጠቀ እንስሳት መካከል ግመልን፣ ጥንቸልንና ሽኮኮን አትብሉ፤ እነርሱ ቢያመሰኩ እንኳ፣ ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ባለመሆኑ፣ በሥርዐቱ መሠረት በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። 8 ዐሣማም እንደዚሁ ርኩስ ነው፤ ምንም እንኳ ሰኰናው የተሰነጠቀ ቢሆንም፣ ስለማያመሰኳ፣ እርሱ ለእናንተ ንጹሕ አይደለም፤ የእነዚህን ሥጋ አትብሉ፤ ጥንባቸውንም አትንኩ። 9 በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ፍጥረታት ሁሉ ክንፍና ቅርፊት ያለውን መብላት ትችላላችሁ፤ 10 ክንፍና ቅርፊት የሌለውን ግን አትብሉ፤ ለእናንተ ርኩስ ነው። 11 ንጹሕ የሆነውን ወፍ ሁሉ መብላት ትችላላችሁ። 12 የሚከተሉትን ግን አትበሉም፤ እነርሱም፦ ንስር፣ የጥንብ አሞራ፣ ግልገል አንሣ፣ 13 ጭልፊት፣ ጭላት፣ ማንኛውም ዐይነት ዐድኖ በል አሞራ፣ 14 ማንኛውም ዐይነት ቍራ፣ 15 ሰጎን፣ ጠላቋ፣ ዝዪ፣ ማንኛውም ዐይነት በቋል፣ 16 ጕጕት፣ ጋጋኖ፣ የውሃ ዶሮ፣ 17 ይብራ፣ ጥንብ አንሣ አሞራ፣ ርኩም፣ 18 ሽመላ፣ ማንኛውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጃንጁላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ ናቸው። 19 ክንፍ ያላቸው ነፍሳት ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ናቸው፤ እነርሱን አትብሏቸው። 20 ንጹሕ የሆነውን ማንኛውንም ክንፍ ያለውን ፍጡር ግን ብሉ። 21 አንተ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ነህና የሞተውን ሁሉ አትብላ፤ ከከተሞችህ በአንዲቱ ለሚኖር መጻተኛ ስጠው፤ ይብላውም፤ ለውጭ አገር ሰው ሽጠው። የፍየልን ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅል። ዐሥራት 22 በየዓመቱ ከዕርሻህ ከምታገኘው ምርት ከዐሥር አንዱን እጅ ለይተህ አስቀምጥ። 23 ምን ጊዜም አምላክህን እግዚአብሔርን ማክበር ትማር ዘንድ፣ የአዲሱን ወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ የቀንድ ከብትህን፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ስፍራ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብላ። 24 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ባርኮህ ሳለ፣ መንገዱ ቢርቅብህና እግዚአብሔር የስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ የሚመርጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ ከመራቁ የተነሣ ዐሥራትህን ወደዚያ ቦታ ማድረስ ካልቻልህ፣ 25 ዐሥራትህን በብር ለውጥ፤ ብሩንም ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ። 26 በብሩም ደስ ያለህን ሁሉ፣ ማለትም የቀንድ ከብት፣ በግ፣ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ ብርቱ መጠጥ ወይም የምትሻውን ሁሉ ግዛበት። ከዚያም አንተና ቤተ ሰብህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በዚያ ትበላላችሁ፤ ሐሤትም ታደርጋላችሁ። 27 የራሱ ድርሻ ወይም ርስት ስለሌለው፣ በከተሞችህ የሚኖረውን ሌዋዊ ቸል አትበለው። 28 በየሦስት ዓመቱ መጨረሻ የዚያን ዓመት ሰብል ዐሥራት በሙሉ አውጥተህ በከተሞችህ ውስጥ አከማች። 29 ይህን የምታደርገው የራሱ ድርሻ ወይም ርስት የሌለው ሌዋዊና መጻተኛ፣ በከተሞችህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች መጥተው እንዲበሉና እንዲጠግቡ፣ አንተንም አምላክህ እግዚአብሔር በእጆችህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.