ዘዳግም 13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሌሎች አማልክትን ማምለክ 1 ነቢይ ወይም ሕልም ዐላሚ ከመካከልህ ተነሥቶ ምልክት ወይም ድንቅ አደርጋለሁ ቢልህ፣ 2 የተናገረው ምልክት ወይም ድንቅ ቢፈጸም፣ “አንተ የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እናምልካቸው” ቢልህ፣ 3 አምላካችሁ እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ ሊፈትናችሁ ነውና፣ የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ሕልም ዐላሚውን አትስማ። 4 አምላካችሁን እግዚአብሔርን ተከተሉት፤ ፍሩት፤ ትእዛዞቹንም ጠብቁ፤ ታዘዙት፤ አገልግሉት፤ ከርሱም ጋራ ተጣበቁ። 5 ከግብጽ ባወጣችሁና ከባርነት ምድር በዋጃችሁ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ላይ እንድታምፁ ተናግሯልና፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንድትከተሉት ካዘዛችሁ መንገድ እንድትመለሱ አድርጓልና፣ ያ ነቢይ ወይም ሕልም ዐላሚ ይገደል፤ ስለዚህ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ። 6 የእናትህ ልጅ ወንድምህ፣ ወንድ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወይም የምትወድዳት ሚስትህ ወይም የልብ ጓደኛህ፣ (አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቋቸውን አማልክት) “ሄደን ሌሎችን አማልክት እናምልክ” ብሎ በስውር ሊያስትህ ቢሞክር፣ 7 በቅርብም ሆነ በሩቅ፣ ከአንዱ የምድር ጫፍ እስከ ሌላው ድረስ በዙሪያህ ያሉትን የአሕዛብ አማልክት እናምልክ ቢልህ፣ 8 ዕሺ አትበለው፤ ወይም አታድምጠው፤ አትራራለት፤ አትማረው፤ ወይም አትሸሽገው። 9 ያለማመንታት ግደለው፤ እርሱንም ለመግደል በመጀመሪያ የአንተ እጅ፣ ከዚያም በኋላ የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይነሣ። 10 የባርነት ምድር ከሆነው ከግብጽ ካወጣህ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ሊያርቅህ ፈልጓልና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው። 11 ከዚያም እስራኤል ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፤ ከመካከልህም ማንም እንደዚህ ያለውን ክፉ ነገር ዳግም አያደርግም። 12 አምላክህ እግዚአብሔር እንድትኖርባቸው ከሚሰጥህ ከተሞች በአንዲቱ ውስጥ እንዲህ ሲባል ብትሰማ፣ 13 ምናምንቴ ሰዎች ከመካከላችሁ ተነሥተው አንተ የማታውቃቸውን፣ “ሌሎች አማልክትን ሄደን እናምልክ” በማለት የከተማቸውን ሕዝብ እያሳቱ ቢሆን፣ 14 ጕዳዩን አጣራ፤ መርምር፤ በሚገባም ተከታተል፤ ነገሩ እውነት ሆኖ ከተገኘና ይህ አስጸያፊ ነገር በመካከልህ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፣ 15 በዚያች ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ በሰይፍ ግደላቸው፤ ከተማዪቱን ከነሕዝቧና ከነቀንድ ከብቷ ፈጽሞ ደምስሳት። 16 በከተማዪቱ የተገኘውን የምርኮ ዕቃ ሁሉ በአደባባይዋ መካከል ላይ ሰብስበህ፣ ከተማዪቱን ከነምርኮዋ እንዳለ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ በሙሉ አቃጥል። ለዘላለም እንደ ፈረሰች ትቅር፤ ተመልሳም አትሠራ። 17 እግዚአብሔር ከብርቱ ቍጣው ይመለስ ዘንድ ዕርም ነገሮች በእጅህ አይገኙ፤ እርሱ ምሕረቱን ያሳይሃል፤ ይራራልሃል፤ ለአባቶችህ በመሐላ ተስፋ በሰጠው መሠረት ቍጥርህን ያበዛዋል፤ 18 ይህም የሚሆነው ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞቹን ሁሉ በመጠበቅና መልካም የሆነውን በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በማድረግ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስለ ታዘዝህለት ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.