ዘዳግም 12 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምብቸኛው የማምለኪያ ስፍራ 1 የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር፣ እንድትወርሷት በሰጣችሁ ምድር ላይ በምትኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ በጥንቃቄ ልትከተሏቸው የሚገባችሁ ሥርዐቶችና ሕግጋት እነዚህ ናቸው። 2 ከምድራቸው የምታስለቅቋቸው አሕዛብ በረዣዥም ተራሮች፣ በኰረብቶችና በእያንዳንዱ ዛፍ ሥር አማልክታቸውን የሚያመልኩባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ። 3 መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቈራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ። 4 በእነርሱ መንገድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አታምልኩ። 5 ዳሩ ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆነው፣ በነገዶቻችሁ መካከል የሚመርጠውን ስፍራ እሹ፤ ወደዚያም ስፍራ ሂዱ። 6 ወደዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ ስእለቶቻችሁንና የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን፣ የቀንድ ከብት መንጋችሁን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አምጡ። 7 በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ትበላላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እናንተን በባረከበት፣ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተ ሰዎችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ። 8 ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፣ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ፤ 9 ምክንያቱም ማረፊያ ወደ ሆነውና አምላካችሁ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ርስት ገና አልደረሳችሁም። 10 ይሁን እንጂ ዮርዳኖስን ስትሻገሩና አምላካችሁ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ስትቀመጡ፣ ያለ ሥጋት እንድትኖሩ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ያሳርፋችኋል። 11 ከዚያም አምላካችሁ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ፣ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፦ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር የተሳላችኋቸውን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ። 12 እዚያም እናንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፣ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ሐሤት አድርጉ። 13 የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በፈለግኸው ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። 14 ከነገዶችህ መካከል በአንዱ፣ እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ ብቻ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችህን አቅርብ፤ እዚያም እኔ የማዝዝህን ሁሉ ጠብቅ። 15 ሆኖም ከአምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ በረከት፣ በየትኛውም ከተማህ፣ እንስሳትህን ሚዳቋም ሆነ ድኵላ ዐርደህ የምትፈልገውን ያህል ሥጋ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነም ሆነ ያልሆነ ሰው ከዚሁ ሥጋ ሊበላ ይችላል። 16 ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 17 የእህልህን፣ የወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት ወይም የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት፣ ወይም ለመስጠት የተሳልኸውን ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታህን፣ ወይም የእጅህን ስጦታ፣ በከተሞችህ ውስጥ መብላት የለብህም። 18 አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችህ፣ በከተሞችህ የሚኖር ሌዋዊም፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበሉታላችሁ፤ እጅህም በነካው ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይልሃል። 19 በምድርም ላይ በምትኖርበት ጊዜ ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትለው ተጠንቀቅ። 20 አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህ፣ ሥጋ አምሮህ፣ “ሥጋ መብላት እፈልጋለሁ” በምትልበት ጊዜ፣ ያሠኘህን ያህል ሥጋ መብላት ትችላለህ። 21 ስሙን ለማኖር አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ የራቀ ከሆነ፣ ባዘዝሁህ መሠረት ከቀንድ ከብትህ፣ ከበግና ከፍየል መንጋህ እንስሳት ማረድ ትችላለህ፤ በከተሞችህ ውስጥ የምትፈልገውን ያህል መብላት ትችላለህ፤ 22 ሚዳቋ ወይም ድኵላ እንደሚበላ አድርገህ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆኑትና ያልሆኑት ሊበሉ ይችላሉ። 23 ደሙን ግን እንዳትበላ ተጠንቀቅ፤ ደም ሕይወት ስለ ሆነ፣ ሥጋን ከነሕይወቱ አትብላ። 24 ደሙን እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 25 በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ መልካም እንዲሆንላቸው አትብላው። 26 ነገር ግን የተቀደሱ ነገሮችህን ለመስጠት የተሳልሃቸውን ሁሉ ይዘህ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ። 27 የሚቃጠል መሥዋዕትህን፣ ሥጋውንም ደሙንም በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አቅርብ። የመሥዋዕትህ ደም በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፤ ሥጋውን ግን መብላት ትችላለህ። 28 በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ ለዘላለም መልካም እንዲሆንላችሁ፣ እኔ የምሰጥህን እነዚህን ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ፈጽማቸው። 29 የምትወርሯቸውንና የምታስለቅቋቸውን አሕዛብ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ባስወጣችኋቸውና በምድራቸው በተቀመጣችሁ ጊዜ ግን፣ 30 ከፊትህ ከጠፉ በኋላ፣ “እነዚህ ሕዝቦች አማልክታቸውን የሚያመልኩት እንዴት ነው? እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ” ብለህ በመጠየቅ እንዳትጠመድ ተጠንቀቅ። 31 አምላክህን እግዚአብሔርን በእነርሱ መንገድ ፈጽሞ አታምልክ፤ ምክንያቱም አማልክታቸውን ሲያመልኩ እግዚአብሔር የሚጸየፈውን ሁሉንም ዐይነት ነገር ያደርጋሉና፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን እንኳ ለአማልክታቸው መሥዋዕት አድርገው ያቃጥላሉ። 32 እኔ ያዘዝሁህን ሁሉ ጠብቅ፤ አትጨምርበት፤ አትቀንስለትም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.