ዘዳግም 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእስራኤል ከኮሬብ እንዲነሡ የተሰጠ ትእዛዝ 1 ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ዓረባ በተባለው ምድረ በዳ ከሱጵ ትይዩ፣ በፋራንና በጦፌል፣ በላባን፣ በሐጼሮትና በዲዛሃብ መካከል ሳሉ፣ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2 (በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ዐሥራ አንድ ቀን ያስሄዳል)። 3 በአርባኛው ዓመት፣ በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን እስራኤላውያንን በሚመለከት እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ሙሴ ለእነርሱ ነገራቸው። 4 ይህ የሆነው በሐሴቦን ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንና በአስታሮት ይገዛ የነበረውን የዐግን ንጉሥ ባሳንን በኤድራይ ድል ካደረገ በኋላ ነው። 5 ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ በሞዓብ ምድር ሳሉ፣ ሙሴ ይህን ሕግ እንዲህ እያለ መግለጥ ጀመረ፤ 6 እግዚአብሔር አምላካችን በኮሬብ እንዲህ አለን፤ “እነሆ፤ በዚህ ተራራ ለረዥም ጊዜ ቈይታችኋል። 7 ሰፈር ነቅላችሁ ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ጕዞ ቀጥሉ፤ ከዚያም በዓረባ፣ በተራሮቹ፣ በምዕራብ ኰረብቶች ግርጌ፣ በኔጌብና በባሕሩ ዳርቻ ወዳሉት አጐራባች ሕዝቦች ሁሉ ሂዱ፤ እንዲሁም ወደ ከነዓናውያን ምድርና ወደ ሊባኖስ፣ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ዝለቁ። 8 እነሆ፤ ይህችን ምድር ሰጥቻችኋለሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ፣ ከእነርሱም በኋላ ለዘሮቻቸው ሊሰጥ የማለላቸውን ምድር ገብታችሁ ውረሱ።” የመሪዎች መሾም 9 እኔም በዚያ ጊዜ እንዲህ አልኋችሁ፤ “ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤ 10 አምላካችሁ እግዚአብሔር ቍጥራችሁን ጨምሯል፤ ስለዚህ ዛሬ እናንተ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችኋል። 11 አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ሺሕ ጊዜ ያብዛችሁ፣ በሰጠውም ተስፋ መሠረት ይባርካችሁ! 12 ይሁን እንጂ ችግራችሁን፣ ሸክማችሁንና ክርክራችሁን ሁሉ ብቻዬን እንዴት አድርጌ መሸከም እችላለሁ? 13 ጥበበኞችን፣ አስተዋዮችንና የተከበሩ ሰዎችን ከየነገዳችሁ ምረጡ፤ እኔም በእናንተ ላይ እሾማቸዋለሁ።” 14 እናንተም፣ “ይደረግ ዘንድ ያቀረብኸው ሐሳብ መልካም ነው” ብላችሁ መለሳችሁልኝ። 15 ስለዚህ እኔም የየነገዶቻችሁን አለቆች ጥበበኞችንና የተከበሩትን ሰዎች ተቀብዬ፣ ሻለቆች፣ መቶ አለቆች፣ ዐምሳ አለቆችና ዐሥር አለቆች እንዲሁም የየነገዱ ሹማምት በማድረግ በእናንተ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ሾምኋቸው። 16 በዚያ ጊዜም ዳኞቻችሁን እንዲህ ስል አዘዝኋቸው፤ “በወንድሞቻችሁ መካከል የሚነሣውን ክርክር ያለ አድልዎ እዩት፤ ሙግቱ ወንድማማች በሆኑ እስራኤላውያን መካከል ወይም በአንድ እስራኤላዊና በመጻተኛ መካከል ቢሆን፣ በጽድቅ ፍረዱ። 17 በፍርድ አድልዎ አታድርጉ፤ ትልቁንም ትንሹንም እኩል እዩ፤ ፍርድ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ ማንኛውንም ሰው አትፍሩ። ከዐቅማችሁ በላይ የሆነውን ሁሉ ወደ እኔ አምጡት፤ እኔ አየዋለሁ።” 18 በዚያ ጊዜ ማድረግ የነበረባችሁን ሁሉ ነገርኋችሁ። የሰላዮች መላክ 19 ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር ባዘዘን መሠረት ከኮሬብ ተነሥተን እንዳያችሁት በዚያ ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ ዐልፈን፣ በኰረብታማው በአሞራውያን አገር በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን። 20 እኔም፣ እንዲህ አልኋችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ደርሳችኋል፤ 21 እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ሰጥቷችኋል፤ አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በነገራችሁ መሠረት ውጡ፤ ውረሷትም፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም።” 22 ከዚያም ሁላችሁ ወደ እኔ መጥታችሁ፣ “ምድሪቱን እንዲሰልሉልን ሰዎች አስቀድመን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያ የሚያደርሰንን መንገድና የምንሄድባቸውን ከተሞች በማጥናት ተመልሰው ይነግሩናል” አላችሁ። 23 ይህም ሐሳብ መልካም መስሎ ታየኝ፤ እኔም ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በማድረግ ከእናንተ ዐሥራ ሁለት ሰዎች መረጥሁ። 24 እነርሱም ተነሥተው ወደ ኰረብታማው አገር ከወጡ በኋላ ወደ ኤሽኮል ሸለቆ መጥተው ምድሪቱን ሰለሉ። 25 ከምድሪቱም ፍሬ ወደ እኛ ይዘው በመምጣት፣ “አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት” ብለው ነገሩን። በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ 26 እናንተ ግን ለመውጣት ፈቃደኞች አልነበራችሁም፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ። 27 በየድንኳኖቻችሁ ሆናችሁ እንዲህ ስትሉ አጕረመረማችሁ፤ “እግዚአብሔር ጠልቶናል፤ ስለዚህም ከግብጽ ያወጣን አሞራውያን እንዲያጠፉን በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ነው። 28 ታዲያ ወዴት መሄድ እንችላለን? ወንድሞቻችን፣ ‘ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎችና ቁመተ ረዣዥሞች፣ ከተሞቹም ትልልቆችና እስከ ሰማይ በሚደርስ ቅጥር የታጠሩ ናቸው፤ እንዲያውም በዚያ የዔናቅን ልጆች አይተናቸዋል’ ሲሉ እንድንፈራ አድርገውናል።” 29 እኔም አልኋችሁ፤ “አትሸበሩ፤ አትፍሯቸውም። 30 በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ዐይናችሁ እያየ በግብጽ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፣ አሁንም ለእናንተ ይዋጋል፤ 31 በምድረ በዳው እንደ አደረገው ሁሉ። በዚያም አባት ልጁን እንደሚሸከም፣ እናንተን አምላካችሁ እግዚአብሔር እዚህ ስፍራ እስክትደርሱ በመጣችሁበት መንገድ ሁሉ እንዴት እንደ ተሸከማችሁ አይታችኋል።” 32 ይህም ሆኖ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር አልታመናችሁም፤ 33 በጕዞ ላይ ሳላችሁ የምትሰፍሩባቸውን ቦታዎች ለመፈለግና የምትሄዱበትን መንገድ ለማሳየት እርሱ ሌሊት በእሳት፣ ቀን በደመና ይመራችሁ ነበር። 34 እግዚአብሔርም እናንተ ያላችሁትን በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ ማለም፤ 35 “ለቀደሙት አባቶቻችሁ ለመስጠት የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር፣ ከዚህ ክፉ ትውልድ አንድም ሰው አያያትም፤ 36 ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በቀር የሚያያት የለም፤ እርሱ ያያታል፤ እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ ስለ ተከተለ፣ የረገጣትን ምድር ለርሱና ለዘሮቹ እሰጣለሁ።” 37 በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔር እኔን ተቈጥቶ እንዲህ አለኝ፤ “አንተም ብትሆን አትገባባትም። 38 ረዳትህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ይገባባታል፤ ምድሪቱን እንዲወርሱ እስራኤልን የሚመራ እርሱ ስለ ሆነ፣ አበረታታው። 39 ይማረካሉ ያላችኋቸው ታናናሾች፣ ክፉና በጎውን ለይተው የማያውቁት ልጆቻችሁ ምድሪቱን ይገቡባታል፤ ለእነርሱም እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሷታል። 40 እናንተ ግን፣ ተመልሳችሁ ወደ ቀይ ባሕር የሚወስደውን መንገድ ይዛችሁ ወደ ምድረ በዳው ተጓዙ።” 41 እናንተ፣ “በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠርተናል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ባዘዘንም መሠረት ወጥተን እንዋጋለን” ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ወደ ተራራማው አገር መሄድ ቀላል መስሎ ስለ ታያችሁ፣ እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያችሁን ታጥቃችሁ ተነሣችሁ። 42 እግዚአብሔር ግን፣ “ ‘እኔ ከእናንተ ጋራ አልሆንምና ወጥታችሁ እንዳትዋጉ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትነሣላችሁ’ ብለህ ንገራቸው” አለኝ። 43 እኔም ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁም፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐምፃችሁ፣ በትዕቢታችሁ ወደ ተራራማው አገር ዘመታችሁ። 44 በእነዚያ በተራራማው አገር የሚኖሩት አሞራውያን ሊወጓችሁ ወጡ፤ እንደ ንብ ሰራዊትም ሆነው አባረሯችሁ፤ ከሴይር አንሥቶ እስከ ሖርማ ድረስ አሳድደው መቷችሁ። 45 እናንተም ተመልሳችሁ መጥታችሁ በእግዚአብሔር ፊት አለቀሳችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ልቅሷችሁን አልሰማም፤ አላደመጣችሁምም። 46 ስለዚህ ያን ያህል ጊዜ በማጥፋት በቃዴስ ብዙ ቀን ቈያችሁ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.