ቈላስይስ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ጌቶች ሆይ፤ እናንተም በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ስለምታውቁ ባሮቻችሁን በፍትሕና በቅንነት አስተዳድሯቸው። ተጨማሪ ምክሮች 2 ከማመስገን ጋራ ነቅታችሁ በትጋት ጸልዩ። 3 እኔ እስረኛ የሆንሁለትን የክርስቶስን ምስጢር ማወጅ እንድንችል፣ እግዚአብሔር የቃሉን በር እንዲከፍትልን ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤ 4 ደግሞም መናገር እንደሚገባኝ ቃሉን በግልጽ እንድናገር ጸልዩልኝ። 5 በውጭ ካሉት ሰዎች ጋራ ባላችሁ ግንኙነት በጥበብ ተመላለሱ፤ በተገኘውም ዕድል ሁሉ ተጠቀሙ። 6 ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን። የስንብት ሰላምታ 7 ቲኪቆስ ስላለሁበት ሁኔታ በሙሉ ይነግራችኋል፤ እርሱ የተወደደ ወንድምና ታማኝ አገልጋይ፣ በጌታም ዐብሮኝ ባሪያ ነው። 8 ስላለንበት ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁንም እንዲያጽናና ለዚህ ጕዳይ ወደ እናንተ እልከዋለሁ፤ 9 እርሱም ከእናንተ ወገን ከሆነው ከታማኙና ከተወዳጁ ወንድማችን ከአናሲሞስ ጋራ ወደ እናንተ ይመጣል፤ እነርሱም እዚህ ስላለው ሁኔታ ሁሉ ይነግሯችኋል። 10 ዐብሮኝ የታሰረው አርስጥሮኮስና የበርናባስ የአክስቱ ልጅ ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ ስለ ማርቆስ መመሪያ ደርሷችኋል፤ እንግዲህ ወደ እናንተ ሲመጣ ተቀበሉት። 11 ኢዮስጦስ የተባለው ኢያሱም ሰላምታ ያቀርብላችኋል። ከተገረዙት መካከል ለእግዚአብሔር መንግሥት ዐብረውኝ የሚሠሩት፣ እኔንም ያጽናኑኝ እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እነርሱም አጽናንተውናል። 12 ከእናንተ ወገን የሆነው የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ እርሱም ፍጹም ጠንክራችሁና ሙሉ በሙሉ ተረጋግታችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ጸንታችሁ እንድትቆሙ ዘወትር ስለ እናንተ በጸሎት እየተጋደለ ነው። 13 ደግሞም ስለ እናንተ እንዲሁም በሎዶቅያና በኢያራ ከተሞች ስላሉት ተግቶ እንደሚሠራ እኔ እመሰክርለታለሁ። 14 የተወደደው ሐኪሙ ሉቃስ እንዲሁም ዴማስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 15 በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞች፣ ለንምፉን፣ በቤቷም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። 16 ይህች መልእክት ከተነበበችላችሁ በኋላ በሎዶቅያ ላለችው ቤተ ክርስቲያን ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ፤ እናንተም ደግሞ በሎዶቅያ ያለችውን መልእክት አንብቡ። 17 ለአርክጳም፣ “በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት ከፍጻሜ ለማድረስ ተጠንቀቅ” በሉልኝ። 18 ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ የጻፍሁት እኔ ጳውሎስ ነኝ። እስራቴን አስቡ። ጸጋ ከእናንተ ጋራ ይሁን። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.