Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሐዋርያት ሥራ 7 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


እስጢፋኖስ በሸንጎው ፊት ያደረገው ንግግር

1 ሊቀ ካህናቱም፣ “ይህ የቀረበብህ ክስ እውነት ነውን?” አለው።

2 እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አድምጡኝ! አባታችን አብርሃም ወደ ካራን ከመምጣቱ በፊት፣ ገና በመስጴጦምያ ሳለ፣ የክብር አምላክ ተገልጦለት፣

3 ‘ከአገርህና ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ’ አለው።

4 “እርሱም ከከለዳውያን ምድር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከአባቱም ሞት በኋላ፣ አሁን እናንተ ወደምትኖሩበት ወደዚህ አገር አመጣው።

5 በዚህም ስፍራ አንዲት ጫማ ታኽል እንኳ ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን በዚያ ጊዜ ምንም ልጅ ሳይኖረው፣ እርሱና ከርሱም በኋላ ዘሩ ምድሪቱን እንደሚወርሱ እግዚአብሔር ቃል ገባለት።

6 ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ‘ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ ይሆናል፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል።

7 ነገር ግን በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እኔ ደግሞ እቀጣዋለሁ፤’ ደግሞም ‘ከዚያም አገር ወጥተው በዚህ ስፍራ ያመልኩኛል።’ ይላል እግዚአብሔር።

8 ከዚያም የግዝረትን ኪዳን ሰጠው፤ አብርሃምም ይሥሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው። ይሥሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የነገድ አባቶች ወለደ።

9 “የነገድ አባቶችም በዮሴፍ ቀንተው በባርነት ወደ ግብጽ ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከርሱ ጋራ ስለ ነበር፣

10 ከመከራው ሁሉ አወጣው፤ በግብጽም ንጉሥ በፈርዖን ፊት ሞገስና ጥበብን አጐናጸፈው፤ ፈርዖንም በግብጽና በቤተ መንግሥቱ ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው።

11 “በዚያ ጊዜም በግብጽና በከነዓን አገር ሁሉ ታላቅ መከራን ያስከተለ ራብ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉትን ዐጡ።

12 ያዕቆብም እህል በግብጽ መኖሩን በሰማ ጊዜ፣ አባቶቻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብጽ ላካቸው፤

13 ለሁለተኛ ጊዜ ሲሄዱ ደግሞ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ገለጠ፤ ፈርዖንም ስለ ዮሴፍ ዘመዶች ተረዳ።

14 ከዚህ በኋላ፣ ዮሴፍ ልኮ አባቱን ያዕቆብንና ሰባ ዐምስት ነፍስ የሚሆኑ ቤተ ዘመዶቹን በሙሉ አስመጣ።

15 ያዕቆብ ወደ ግብጽ ወረደ፤ እርሱም አባቶቻችንም በዚያ ሞቱ።

16 አስከሬናቸውም ወደ ሴኬም ተወስዶ፣ አብርሃም ከዔሞር ልጆች ላይ በጥሬ ብር በገዛው መቃብር ተቀበረ።

17 “እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ሲቃረብም፣ በግብጽ የነበረው የሕዝባችን ቍጥር እየበዛ ሄደ።

18 ከዚያ በኋላ ‘ስለ ዮሴፍ የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብጽ ነገሠ።’

19 እርሱም ሕዝባችንን በተንኰሉ አስጨነቀ፤ ገና የተወለዱ ሕፃናታቸውም ይሞቱ ዘንድ ወደ ውጭ አውጥተው እንዲጥሏቸው አስገደዳቸው።

20 “በዚህ ጊዜ ሙሴ ተወለደ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘ ውብ ሕፃን ነበር። በአባቱም ቤት ሦስት ወር በእንክብካቤ አደገ።

21 ወደ ውጭ በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አግኝታ ወሰደችው፤ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋም አሳደገችው።

22 ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በንግግሩና በተግባሩም ብርቱ ሆነ።

23 “ሙሴ አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ፣ ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ሊጐበኝ በልቡ ዐሰበ።

24 እርሱም፣ አንድ ግብጻዊ ከወገኖቹ አንዱን በደል ሲያደርስበት አይቶ ግብጻዊውንም ገደለ፤ ለተገፋው ወገኑም ተበቀለ።

25 ወገኖቹም እግዚአብሔር በርሱ እጅ ነጻ እንደሚያወጣቸው የሚያስተውሉ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።

26 በማግስቱም ደግሞ ሁለት እስራኤላውያን ሲጣሉ ደረሰ፤ ሊያስታርቃቸውም ፈልጎ፣ ‘ሰዎች፤ እናንተ እኮ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እንዴት እርስ በርሳችሁ ትጐዳዳላችሁ?’ አላቸው።

27 “በባልንጀራው ላይ በደል ሲያደርስ የነበረው ሰው ግን፣ ሙሴን ገፈተረውና እንዲህ አለ፤ ‘አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው?

28 ትናንት ግብጻዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋልህን?’

29 ሙሴም ይህን እንደ ሰማ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ተቀመጠ፤ በዚያም ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ።

30 “ከአርባ ዓመት በኋላ፣ በሲና ተራራ አካባቢ ባለው ምድረ በዳ፣ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መልአክ ተገለጠለት።

31 ሙሴም ባየው ነገር ተደነቀ፤ ነገሩን ለማጣራት ወደዚያ ሲቀርብ የጌታ ድምፅ፤

32 ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይሥሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ሲል ሰማ። ሙሴም በፍርሀት ተዋጠ፤ ለመመልከትም አልደፈረም።

33 “ጌታም እንዲህ አለው፤ ‘የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማውን ከእግርህ አውልቅ፤

34 በግብጽ ያለውን የሕዝቤን መከራ በርግጥ አይቻለሁ፤ የጭንቅ ጩኸታቸውን ሰምቻለሁ፤ ላድናቸውም ወርጃለሁ። አሁንም ና፤ ወደ ግብጽ መልሼ እልክሃለሁ።’

35 “እንግዲህ እነዚያ፣ ‘አንተን ገዥና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው?’ ብለው የናቁትን ይህን ሙሴ እግዚአብሔር በቍጥቋጦው ውስጥ በታየው መልአክ አማካይነት ገዥና ታዳጊ አድርጎ ወደ እነርሱ ላከው።

36 እርሱም መርቶ ከግብጽ አወጣቸው፤ በግብጽ፣ በቀይ ባሕርና በምድረ በዳ አርባ ዓመት ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን አደረገ።

37 “የእስራኤልንም ልጆች፣ ‘እግዚአብሔር እንደ እኔ ያለ ነቢይ ከወንድሞቻችሁ መካከል ያስነሣላችኋል’ ያላቸው ይኸው ሙሴ ነበር።

38 እርሱም በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋራ በምድረ በዳ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ነበር፤ የሕይወትንም ቃል ወደ እኛ ለማስተላለፍ ተቀበለ።

39 “አባቶቻችን ግን ተቃወሙት እንጂ ሊታዘዙት ስላልፈለጉ በልባቸው ወደ ግብጽ ተመለሱ።

40 አሮንንም፣ ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅምና!’ አሉት።

41 በዚያ ጊዜ የጥጃ ምስል ሠርተው፣ ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ተደሰቱ፤ ፈነጠዙም።

42 እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ ዘወር አለ፤ ያመልኳቸውም ዘንድ ለሰማይ ከዋክብት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም በነቢያት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ተፈጸመ፤ “ ‘እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ፣ መሥዋዕትንና ቍርባንን አቅርባችሁልኝ ነበርን?

43 ይልቁንም ልታመልኳቸው የሠራችኋቸውን፣ የሞሎክን ድንኳንና የኮከብ አምላክ የሆነውን የሬምፋም ጣዖት አንሥታችሁ ተሸከማችሁ። ስለዚህ ከባቢሎን ማዶ እንድትጋዙ አደርጋለሁ።’

44 “እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው ንድፍና ባዘዘው መሠረት የተሠራችው የምስክር ድንኳን፣ ከአባቶቻችን ጋራ በምድረ በዳ ነበረች።

45 አባቶቻችንም ድንኳኗን ከተቀበሉ በኋላ፣ እግዚአብሔር በኢያሱ መሪነት ያሳደዳቸውን የአሕዛብን አገር በወረሱ ጊዜ ይዘዋት ገቡ፤ እስከ ዳዊትም ዘመን ድረስ በምድሪቱ ተቀመጠች፤

46 ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ በማግኘቱ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ያዘጋጅ ዘንድ ለመነ፤

47 ነገር ግን የማደሪያውን ቤት የሠራለት ሰሎሞን ነበር።

48 “ይሁን እንጂ፣ ልዑል የሰው እጅ በሠራው ቤት ውስጥ አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ባለው መሠረት ነው፤

49 “ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤ ታዲያ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ? ይላል ጌታ፤ ወይስ ማረፊያ የሚሆነኝ ቦታ የት ነው?

50 እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን?’

51 “እናንተ ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ! ዐንገተ ደንዳኖች ልክ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ሁልጊዜ ትቃወማላችሁ።

52 ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን እንኳ ገድለዋል፤ እናንተም አሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም፤

53 በመላእክት አማካይነት የተሰጣችሁንም ሕግ ተቀበላችሁ እንጂ አልጠበቃችሁትም።”


የእስጢፋኖስ መወገር

54 በሸንጎው ስብሰባ ላይ የነበሩትም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።

55 እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣

56 “እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።

57 በዚህ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ጆሯቸውን ደፍነው እርሱ ወደ አለበት በአንድነት ሮጡ፤

58 ይዘውም ከከተማው ውጭ ጣሉት፤ በድንጋይም ይወግሩት ጀመር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በዚያ የነበሩ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በተባለ ጕልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ።

59 እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ነፍሴን ተቀበላት፤” ብሎ ጸለየ፤

60 ከዚያም ተንበርክኮ በታላቅ ድምፅ፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው!” ብሎ ጮኸ፤ ይህን ካለ በኋላም አንቀላፋ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告