Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሐዋርያት ሥራ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ጴጥሮስ ሽባውን ለማኝ ፈወሰ

1 አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ጊዜ፣ ይኸውም ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር።

2 ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት እንዲለምን፣ ሰዎች በየዕለቱ ተሸክመው “ውብ” በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ የሚያስቀምጡት አንድ ከተወለደ ጀምሮ ሽባ የሆነ ሰው ነበረ፤

3 እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው።

4 ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋራ ወደ እርሱ ትኵር ብሎ አየውና፣ “እስኪ ወደ እኛ ተመልከት!” አለው።

5 ሰውየውም፣ ከእነርሱ አንድ ነገር ለማግኘት ዐስቦ በትኵረት ተመለከታቸው።

6 ጴጥሮስ ግን፣ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ነገር ግን ያለኝን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ በእግርህ ተመላለስ” አለው፤

7 ቀኝ እጁንም ይዞ አስነሣው፤ ወዲያውም እግሩና ቍርጭምጭሚቱ በረታ፤

8 ዘልሎም ቀጥ ብሎ ቆመ፤ መራመድም ጀመረ፤ ወዲህ ወዲያ እየሄደና እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋራ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገባ።

9 ሕዝቡም ሁሉ እየተራመደና እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ ባዩት ጊዜ፣

10 ይህ ሰው ቀደም ሲል “ውብ” በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እርሱ መሆኑን ዐወቁ፤ በርሱ ላይ ከተፈጸመውም ነገር የተነሣ በመደነቅና በመገረም ተሞሉ።


ጴጥሮስ ሰውየው ሲፈወስ ላየው ሕዝብ ንግግር አደረገ

11 የተፈወሰውም ሰው ከጴጥሮስና ዮሐንስ ጋራ ጥብቅ ብሎ ዐብሯቸው ሳለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በመገረም እነርሱ ወደ ነበሩበት “የሰሎሞን መመላለሻ” ወደተባለው ስፍራ እየሮጡ መጡ።

12 ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ በዚህ ለምን ትደነቃላችሁ? ደግሞም በእኛ ኀይል ወይም በእኛ ጽድቅ ይህ ሰው ድኖ እንዲመላለስ እንዳደረግነው በመቍጠር፣ ለምን ወደ እኛ አትኵራችሁ ትመለከታላችሁ?

13 የአባቶቻችን አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እንዲሞት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስ ሊፈታው ቢፈልግም እናንተ በርሱ ፊት ካዳችሁት፤

14 ቅዱሱንና ጻድቁን ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ፤

15 የሕይወት መገኛ የሆነውን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ እኛም ለዚህ ምስክሮች ነን።

16 ይህ የምታዩትና የምታውቁት ሰው የበረታው በኢየሱስ ስም በማመን ነው፤ ሁላችሁም እንደምታዩት ፍጹም ፈውስ እንዲያገኝ ያደረገው የኢየሱስ ስምና በርሱ አማካይነት የሚገኘው እምነት ነው።

17 “አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ እናንተ ይህን ያደረጋችሁት እንደ አለቆቻችሁ ሁሉ ባለማወቅ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ።

18 እግዚአብሔር ግን የርሱ የሆነው ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያቱ ሁሉ አፍ የተናገረውን ፈጽሟል።

19 እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፤ ከጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤

20 ደግሞም አስቀድሞ ለእናንተ የተመደበውን ክርስቶስን፣ እርሱም ኢየሱስን ይልክላችኋል።

21 እግዚአብሔር አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፣ ሁሉን ነገር እስከሚያድስበት ዘመን ድረስ እርሱ በሰማይ ይቈይ ዘንድ ይገባል።

22 ሙሴም እንዲህ ብሏል፤ ‘ጌታ አምላካችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ከወንድሞቻችሁ መካከል ያስነሣላችኋል፤ እርሱ የሚነግራችሁን ሁሉ ስሙት፤

23 ያን ነቢይ የማትሰማ ነፍስ ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይታ ትጥፋ።’

24 “በርግጥም ከሳሙኤል ጀምሮ የተነሡት ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ጊዜያት ተናግረዋል።

25 እናንተም የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ ‘በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎ የገባው ኪዳን ወራሾች ናችሁ።

26 እግዚአብሔር ብላቴናውን ባስነሣ ጊዜ፣ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ መልሶ ይባርካችሁ ዘንድ አስቀድሞ ወደ እናንተ ላከው።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告