2 ጢሞቴዎስ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት፣ መገለጡንና መንግሥቱን በማሰብ ይህን ዐደራ እልሃለሁ፤ 2 ቃሉን ስበክ፤ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ ገሥጽ፤ አበረታታም፤ 3 ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሯቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። 4 እውነትን ከመስማት ጆሯቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ። 5 አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም። 6 እኔ እንደ መጠጥ ቍርባን መሥዋዕት ለመፍሰስ ተቃርቤአለሁ፤ ተለይቼ የምሄድበትም ጊዜ ደርሷል። 7 መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ። 8 ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው። የጳውሎስ ማሳሰቢያ 9 በቶሎ ወደ እኔ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ 10 ዴማስ ይህን ዓለም ወድዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዷልና። ቄርቂስ ወደ ገላትያ፣ ቲቶ ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤ 11 ከእኔ ጋራ ያለው ሉቃስ ብቻ ነው። ማርቆስ በአገልግሎቴ ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋራ ይዘኸው ና። 12 ቲኪቆስን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ። 13 ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖስ፣ ጥቅልል መጻሕፍቱን፣ በተለይም የብራና መጻሕፍቱን አምጣልኝ። 14 አንጥረኛው እስክንድሮስ ብዙ ጕዳት አድርሶብኛል፤ ጌታ ግን የእጁን ይሰጠዋል። 15 መልእክታችንን እጅግ ተቃውሟልና፤ አንተም ከርሱ ተጠንቀቅ። 16 በተከሰስሁበት ነገር የመጀመሪያ መከላከያዬን ሳቀርብ ማንም ሊያግዘኝ አልመጣም፤ ነገር ግን ሁሉ ትተውኝ ሄዱ። ይህንም አይቍጠርባቸው። 17 ነገር ግን መልእክቱ በእኔ አማካይነት በሙላት እንዲሰበክና አሕዛብ ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ በአጠገቤ ቆሞ አበረታኝ፤ ከአንበሳም መንጋጋ አዳነኝ። 18 ጌታ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ወደ ሰማያዊው መንግሥቱም በሰላም ያደርሰኛል፤ ለርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን። አሜን። የስንብት ሰላምታ 19 ለጵርስቅላና ለአቂላ፣ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ። 20 ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀርቷል፤ ጥሮፊሞስም ስለ ታመመ በሚሊጢን ትቼዋለሁ። 21 ከክረምት በፊት እዚህ ለመምጣት የተቻለህን አድርግ። ኤውግሎስና ጱዴስ እንዲሁም ሊኖስ፣ ቅላውዲያና ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። 22 ጌታ ከመንፈስህ ጋራ ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋራ ይሁን። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.