Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ተሰሎንቄ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የዐመፅ ሰው

1 ወንድሞች ሆይ፤ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱም ስለ መሰብሰባችን ይህን እንለምናችኋለን፤

2 በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደ ተላከ መልእክት የጌታ ቀን ደርሷል ብላችሁ ፈጥናችሁ ከአእምሯችሁ አትናወጡ፤ አትደንግጡም።

3 ማንም ሰው በምንም መንገድ አያታልላችሁ፤ አስቀድሞ ዐመፅ ሳይነሣ፣ ለጥፋት የተመደበውም የዐመፅ ሰው ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣምና።

4 እርሱም አምላክ ከተባለና ከሚመለከው ነገር ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቀምጦ፣ “እኔ አምላክ ነኝ” እያለ ዐዋጅ ያስነግራል።

5 ከእናንተ ጋራ በነበርሁበት ጊዜ፣ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችሁ እንደ ነበር ትዝ አይላችሁምን?

6 በራሱ ጊዜ ይገለጥ ዘንድ አሁን ምን እንደሚከለክለው ታውቃላችሁ።

7 የዐመፅ ምስጢር አሁንም እንኳ እየሠራ ነውና፤ ነገር ግን ይህ የሚሆነው የሚከለክለው ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ ብቻ ነው።

8 ከዚያም በኋላ ጌታ ኢየሱስ በአፉ እስትንፋስ የሚያስወግደውና በምጽአቱም ክብር ፈጽሞ የሚያጠፋው ዐመፀኛ ይገለጣል።

9 የእርሱም አመጣጥ እንደ ሰይጣን አሠራር ሲሆን፣ ይህም በኀይል ሁሉ፣ በሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቆችም ሁሉ ይሆናል፤

10 እንዲሁም ይድኑ ዘንድ እውነትን ባለመውደድ የሚጠፉትን ሰዎች በሚያታልል በተለያየ የክፋት ሥራ ይመጣል።

11 በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር በሐሰት እንዲያምኑ የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል፤

12 ይህም የሚሆነው እውነትን ያላመኑት ነገር ግን በክፋት ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ እንዲፈረድባቸው ነው።


ጸንታችሁ ቁሙ

13 በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ ግን ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ልናመሰግን ይገባናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር እናንተን ከመጀመሪያ አንሥቶ በመንፈስ ተቀድሳችሁና በእውነትም አምናችሁ እንድትድኑ መርጧችኋል።

14 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ተካፋዮች እንድትሆኑም በወንጌላችን አማካይነት ጠርቷችኋል።

15 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በአንደበታችንም ሆነ በመልእክታችን ያስተላለፍንላችሁን ትምህርት አጥብቃችሁ ያዙ።

16 ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ደግሞም እኛን የወደደንና በጸጋው የዘላለም መጽናናትና መልካም ተስፋን የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን፣

17 ልባችሁን ያጽናኑት፤ በበጎ ሥራና በቃል ሁሉ ያበርቷችሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告