2 ነገሥት 25 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መላ ሰራዊቱን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ዘመተ፤ ከከተማዪቱ ቅጥር ውጭ ሰፈረ፤ ዙሪያውንም በሙሉ በዕርድ ከበባት። 2 ከተማዪቱም እስከ ንጉሥ ሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት ዐሥራ አንደኛ ዓመት ድረስ እንዲሁ እንደ ተከበበች ቈየች። 3 በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ውስጥ የተከሠተው ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚቀምሰው ዐጣ። 4 ምንም እንኳ ባቢሎናውያን ከተማዪቱን እንደ ከበቧት ቢሆንም የከተማዪቱ ቅጥር ተጣሰ፤ ሰራዊቱም ሁሉ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ባሉት በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በዓረባ በር ዐልፎ በሌሊት ሸሸ፤ ሽሽቱም ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ ነበር። 5 ይሁን እንጂ የባቢሎናውያንም ሰራዊት ንጉሡን ተከታትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ ሜዳ ላይ ደረሱበት። ወታደሮቹም ሁሉ ተለይተውት ተበታትነው ሳለ 6 ንጉሡን ያዙት። በዚያ ጊዜ ሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ በዚያም የባቢሎን ንጉሥ ፈረደበት። 7 ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየም ወንዶች ልጆቹን ገደሉበት፤ ከዚያም ሁለት ዐይኖቹን በማውጣት በናስ ሰንሰለት አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 8 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት፣ በዐምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ባለሟል የክብር ዘበኞች አዛዥ የነበረው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 9 የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ ቤተ መንግሥቱን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የሚገኙትን ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እያንዳንዱንም ትልልቅ ሕንጻዎችንም በእሳት አወደመ። 10 በክብር ዘቡ አዛዥ የተመራው መላው የባቢሎን ሰራዊትም በኢየሩሳሌም ዙሪያ የነበረውን ቅጥር አፈረሰው። 11 የክብር ዘቡ አዛዥ ናቡዘረዳን ድኾችንና በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብና ሸሽተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን አፈለሳቸው። 12 ሆኖም የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ሌሎች የምድሪቱን ድኾች፣ ወይን ተካዮችና ዐራሾች እንዲሆኑ አስቀራቸው። 13 ባቢሎናውያን የናስ ዐምዶቹን፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበሩትን ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ሰባበሩ፤ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 14 እንዲሁም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ጭልፋዎቹን፣ በአጠቃላይም ከናስ የተሠሩትን የቤተ መቅደሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ። 15 የክብር ዘቡ አዛዥም ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን ጥናዎችና የመርጫ ወጭቶችን ወሰደ። 16 ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ ብሎ ከናስ ያሠራቸው ሁለት ዐምዶች፣ ትልቁ የውሃ ገንዳ፤ ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎች ክብደታቸው ከሚዛን በላይ ነበር። 17 እያንዳንዱም ዐምድ ከፍታው ዐሥራ ስምንት ክንድ ሲሆን፣ የናስ ጕልላት ነበረው፤ የጕልላቱ ርዝመት ሦስት ክንድ ሆኖ፣ ዙሪያውን በሙሉ የናስ መርበብና የሮማን ፍሬዎች ቅርጽ ነበረው፤ ሌላውም ዐምድ ከነቅርጾቹ ከዚሁ ጋራ ተመሳሳይ ነበር። 18 የክብር ዘበኞቹ አዛዥም ሊቀ ካህኑን ሠራያን፣ በማዕርግ ከርሱ ቀጥሎ ያለውን ካህኑን ሶፎንያስንና ሦስቱን የበር ጠባቂዎች እስረኛ አድርጎ ወሰዳቸው። 19 እስከዚያች ጊዜ ድረስ በከተማዪቱ ውስጥ ከቀሩትም የተዋጊዎቹን አለቃና ዐምስት የንጉሡን አማካሪዎች ወሰዳቸው። ደግሞም የአገሩን ሕዝብ ለውትድርና የሚመለምለውን ዋና የጦር አለቃ የነበረውን ጸሓፊውንና በከተማዪቱ ውስጥ የተገኙትን የጸሓፊውን ስድሳ ሰዎች ወሰዳቸው። 20 የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ነበረበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። 21 ንጉሡም ሰዎቹን በሐማት ምድር በነበረችው በሪብላ ውስጥ አስገደላቸው። ይሁዳም ከምድሩ በዚህ ሁኔታ ተማርኮ ሄደ። 22 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ የሳፋን ልጅ የሆነውን የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስን እዚያው በቀረው በይሁዳ ሕዝብ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። 23 መላው የሰራዊቱ ጦር አለቆችና ሰዎቻቸው የባቢሎን ንጉሥ፣ አገረ ገዥ አድርጎ ጎዶልያስን መሾሙን ሲሰሙ፣ እርሱ ወዳለበት ወደ ምጽጳ መጡ፤ እነርሱም የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፣ የነጦፋዊው የተንሑሜት ልጅ ሠራያ የማዕካታዊው ልጅ ያእዛንያና ሰዎቻቸው ነበሩ። 24 ጎዶልያስም፣ “የባቢሎናውያንን ሹማምት አትፍሩ፤ እዚሁ አገር ኑሩ፤ የባቢሎንን ንጉሥ አገልግሉ፤ ሁሉም ነገር ይሳካላችኋል” ሲል ይህንኑ በቃለ መሐላ አረጋገጠላቸው። 25 ነገር ግን በሰባተኛው ወር ንጉሣዊ ዝርያ የነበረው የኤሊሳማ የልጅ ልጅ የሆነው የናታንያ ልጅ እስማኤል ዐሥር ሰዎች ይዞ መጥቶ ጎዶልያስንና በምጽጳ ዐብረውት የነበሩትን የይሁዳን ሰዎችና ባቢሎናውያንን ገደለ። 26 ባቢሎናውያንን ከመፍራታቸው የተነሣም ትንሽ ትልቅ ሳይባል ሕዝቡ ሁሉ ከሰራዊቱ የጦር አለቆች ጋራ ወደ ግብጽ ሸሹ። ዮአኪን ከእስራት ተፈታ 25፥27-30 ተጓ ምብ – ኤር 52፥31-34 27 የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ ሰባተኛው ቀን ዮርማሮዴክ በባቢሎን በነገሠ በዓመቱ ዮአኪንን ከወህኒ ፈታው። 28 በመልካምም ቃል አናገረው፤ ከርሱም ጋራ በባቢሎን በምርኮ ከነበሩት ነገሥታት ይልቅ ከፍ ባለ የክብር ቦታ አስቀመጠው። 29 ዮአኪንም የእስር ቤት ልብሱን ጣለ፤ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማእድ ዘወትር ይመገብ ነበር፤ 30 ንጉሡም ለዮአኪን እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ የዕለት ቀለቡን ይሰጠው ነበር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.