Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ነገሥት 24 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ምድሪቱን ወረረ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ገበረለት፤ ከዚያ በኋላ ግን ሐሳቡን ለውጦ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ።

2 እግዚአብሔርም በኢዮአቄም ላይ ባቢሎናውያን፣ ሶርያውያን፣ ሞዓባውያንና አሞናውያን አደጋ ጣዮችን ላከበት፤ በአገልጋዮቹ በነቢያቱ አማካይነት በተነገረው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ይሁዳን ያጠፉ ዘንድ እነዚህን ላከ።

3 ከፊቱ ያርቃቸው ዘንድ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በይሁዳ ላይ በትክክል ሊፈጸሙ ችለዋል፤ ይህም ምናሴ ስለ ሠራው ኀጢአትና ስለ ፈጸመውም ሁሉ፣

4 እንዲሁም ንጹሕ ደም ስላፈሰሰ ነው። ኢየሩሳሌምም በንጹሕ ደም እንድትጥለቀለቅ በማድረጉ፤ እግዚአብሔር ይቅርታ ለማድረግ አልፈለገም።

5 በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

6 ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ዮአኪንም በምትኩ ነገሠ።

7 የባቢሎንም ንጉሥ ከግብጽ ደረቅ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ የነበረውን ግዛቱን ሁሉ ወስዶበት ስለ ነበር፣ የግብጽ ንጉሥ ከአገሩ ዳግም ለዘመቻ አልወጣም።


የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን
24፥8-17 ተጓ ምብ – 2ዜና 36፥9-10

8 ዮአኪን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ወር ገዛ። እናቱ ኔስታ ትባላለች፤ እርሷም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች።

9 አባቱ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

10 በዚያ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነፆር ጦር አለቆች ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መጥተው ከበቧት፤

11 የጦር አለቆቹ ከበባ በሚያደርጉበትም ሰዓት ንጉሥ ናቡከደነፆር ራሱ ወደ ከተማዪቱ መጣ።

12 የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን፣ እናቱ፣ የክብር አጃቢዎቹ፣ መሳፍንቱና ሹማምቱ ሁሉ እጃቸውን ለባቢሎን ንጉሥ ሰጡ። የባቢሎን ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ዮአኪንን ማርኮ ወሰደው።

13 እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደ ተናገረው፣ ናቡከደነፆር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሀብት በሙሉ አጋዘ፤ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያሠራቸውንም የወርቅ ዕቃዎች ሁሉ ወሰደ።

14 ደግሞም የኢየሩሳሌምን ሕዝብ እንዳለ የጦር አለቆቹንና ተዋጊዎቹን በሙሉ፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ቀጥቃጮችን ሁሉ ጨምሮ በአጠቃላይ ዐሥር ሺሕ ሰው በምርኮ ወደ አገሩ ወሰደ። በዚያ የቀሩት የመጨረሻዎቹ ያገሪቱ ድኾች ብቻ ነበሩ።

15 ናቡከደነፆር ዮአኪንን ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ እንዲሁም የንጉሡን እናት፣ ሚስቶቹን፣ ሹማምቱና በአገር የታወቁትን ታላላቅ ሰዎችም ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ወሰደ።

16 ደግሞም የባቢሎን ንጉሥ በአጠቃላይ ብርቱ የሆኑትንና ለጦርነት ብቃት ያላቸውን ሰባት ሺሕ ተዋጊዎች፣ አንድ ሺሕ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ቀጥቃጮችን በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደ።

17 ከዚያም የዮአኪንን አጎት ማታንያን በምትኩ አነገሠው፤ ስሙንም ሴዴቅያስ ብሎ ለወጠው።


የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ
24፥18-20 ተጓ ምብ – 2ዜና 36፥11-16 ፤ ኤር 52፥1-3

18 ሴዴቅያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ። የእናቱም ስም አሚጣል ነበረ፤ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።

19 ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።

20 እንግዲህ ይህ ሁሉ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሊደርስ የቻለው ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ነበር፤ በመጨረሻም ከፊቱ አስወገዳቸው። በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告