2 ነገሥት 19 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምኢየሩሳሌም ከጠላት እጅ እንደምትድን አስቀድሞ መነገሩ 19፥1-13 ተጓ ምብ – ኢሳ 37፥1-13 1 ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለበሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ገባ። 2 ከዚያም የቤተ መንግሥቱን አዛዥ ኤልያቄምን፣ ጸሓፊውን ሳምናስንና ከካህናቱ ዋና ዋናዎቹን ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው። 3 እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ‘ይህ ቀን የጭንቀት፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው፤ ልጆች ሊወለዱ ሲሉ ብርታት እንደሚታጣበት ቀን ሆኗል። 4 ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የጦር አዛዡን ቃል እግዚአብሔር አምላክህ ይሰማ ይሆናል፤ እግዚአብሔር አምላክህም ሰምቶ ይገሥጸው ይሆናል፤ ስለዚህ አንተም በሕይወት ለተረፉት ቅሬታዎች ጸልይ።’ ” 5 የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳይያስ መጡ፤ 6 ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች እኔን ስለ ሰደቡኝ፣ በሰማኸው ቃል አትሸበር። 7 እነሆ፤ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፤ ወሬም ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።’ ” 8 የጦር አዛዡም የአሦር ንጉሥ ለኪሶን ትቶ መሄዱን ሲሰማ ተመለሰ፤ ንጉሡም ልብናን ሲወጋ አገኘው። 9 ደግሞም ሰናክሬም፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋው መምጣቱን ሰማ፤ ይህንም እንደ ሰማ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤ 10 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ አትያዝም’ ብሎ የተማመንህበት አምላክ አያታልልህ። 11 እነሆ፤ የአሦር ነገሥታት በአገሮች ሁሉ ላይ ያደረጉትን፣ ፈጽሞም እንዳጠፏቸው ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 12 የቀደሙት አባቶቼ ያጠፏቸውን፣ የጎዛንን፣ የካራንን፣ የራፊስን እንዲሁም በተላሳር የሚኖሩ የዔድንን ሰዎች የአሕዛብ አማልክት አድነዋቸዋልን? 13 የሐማት ንጉሥ፣ የአርፋድ ንጉሥ፣ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፣ የሄና ንጉሥ ወይም የዒዋ ንጉሥ የት አሉ?” የሕዝቅያስ ጸሎት 19፥14-19 ተጓ ምብ – ኢሳ 37፥14-20 14 ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጥቶም ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። 15 ሕዝቅያስም እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ “በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል። 16 አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህን ክፈትና እይ፤ ሰናክሬም ሕያው እግዚአብሔርን ለመሳደብ የላከውን ቃል ስማ። 17 “እግዚአብሔር ሆይ፤ የአሦር ነገሥታት እውነትም እነዚህን አሕዛብንና ምድራቸውን አጥፍተዋል። 18 አማልክታቸውን በእሳት ውስጥ ጥለው አቃጥለዋቸዋል፤ በሰው እጅ የተሠሩ ዕንጨትና ድንጋይ ብቻ እንጂ አማልክት አልነበሩምና። 19 አሁንም እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ መሆንህን ያውቁ ዘንድ፣ ከእጁ አድነን።” ኢሳይያስ ስለ ሰናክሬም መውደቅ ትንቢት ተናገረ 19፥35-37 ተጓ ምብ – 2ዜና 32፥20-21 20 ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በአሦር ንጉሥ በሰናክሬም ላይ ወደ እኔ ያቀረብኸውን ልመና ሰምቻለሁ’ 21 እንግዲህ እግዚአብሔር በርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ “ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፣ ንቃሃለች፤ ታቃልልሃለችም፤ የኢየሩሳሌም ልጅ፣ አንተ ስትሸሽ ራሷን ነቅንቃብሃለች። 22 ለመሆኑ የሰደብኸውና ያቃለልኸው ማንን ነው? ድምፅህንስ ከፍ ያደረግኸው? ዐይንህንስ በኵራት ያነሣኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው እንዴ? 23 በመልእክተኞችህ በኩል፣ በጌታ ላይ የስድብ ቃል ተናገርህ፤ እንዲህም አልህ፤ “በሠረገሎቼ ብዛት፣ የተራሮችንም ከፍታ፣ የሊባኖስንም ጫፍ ወጥቻለሁ፤ ረዣዥም ዝግባዎችን፣ የተመረጡ ጥዶችን ቈርጫለሁ፤ እጅግ ወደራቁት፣ እጅግ ውብ ወደሆኑትም ደኖች ደርሻለሁ። 24 በባዕድ ምድር የውሃ ጕድጓዶችን ቈፈርሁ፤ በዚያም ውሃ ጠጣሁ። የግብጽን ምንጮች ሁሉ፣ በእግሬ ረግጬ አደረቅሁ።” 25 “ ‘ይህን ቀድሞ እንደ ወሰንሁት፣ አልሰማህምን? ጥንትም እንዳቀድሁት፣ አሁን ግን እንዲፈጸም አደረግሁት፤ ይህም የተመሸጉትን ከተሞች፣ አንተ የድንጋይ ክምር ማድረግህ ነው። 26 የሚኖሩባቸውም ሰዎች ኀይላቸው ተሟጥጦ ዐልቋል፤ ደንግጠውም የኀፍረት ማቅ ለብሰዋል፤ ሜዳ ላይ እንደ በቀለ ተክል፣ ገና እንዳልጠነከረ የቡቃያ ሥር፣ በቤት ጣራ ላይ በቅሎ፣ ገና ሳያድግ እንደ ጠወለገ ሣርም ሆነዋል። 27 “ ‘እኔ ግን የት እንዳለህ፣ መቼ እንደምትመጣና መቼ እንደምትሄድ፣ በእኔም ላይ እንዴት በቍጣ እንደምትነሣሣ ዐውቃለሁ። 28 በእኔ ላይ በቍጣ ስለ ተነሣሣህ፣ እብሪትህም ወደ ጆሮዬ ስለ ደረሰ፣ ስናጋዬን በአፍንጫህ አደርጋለሁ፤ ልጓሜን በአፍህ አስገባለሁ፤ በመጣህበትም መንገድ እንድትመለስ አደርግሃለሁ።’ 29 “ሕዝቅያስ ሆይ፤ ምልክቱ ይህ ነው፤ “በዚህ ዓመት በገዛ እጁ የበቀለውን፣ በሚመጣው ዓመት ደግሞ የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁ፤ ወይንም ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ። 30 አሁንም ከይሁዳ ቤት የተረፉት፣ ሥራቸውን ወደ ታች ይሰድዳሉ፤ ወደ ላይም ፍሬ ያፈራሉ። 31 ቅሬታ የሆኑት ከኢየሩሳሌም፣ የተረፉትም ከጽዮን ተራራ ይመጣሉና። የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል። 32 “ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ “ ‘ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባም፤ ፍላጻም አይወረውርባትም፤ ጋሻ አንግቦ አይቀርብም፤ በዐፈርም ቍልል አይከብባትም። 33 በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤ ወደዚህች ከተማም አይገባም’ ይላል እግዚአብሔር። 34 ‘ስለ ራሴና ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል፣ ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ፤ አድናታለሁም።’ ” 35 በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፤ ከአሦራውያን ሰፈር አንድ መቶ ሰማንያ ዐምስት ሺሕ ሰው ገደለ፤ ሰዎቹ ማለዳ ሲነሡ፤ ቦታው ሬሳ በሬሳ ነበር። 36 ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ነነዌም ተመልሶ በዚያ ተቀመጠ። 37 ናሳራክ በተባለው አምላኩ ቤተ ጣዖት ገብቶ በመስገድ ላይ ሳለ፣ አድራሜሌክና ሳራሳር የተባሉ ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት፤ ከዚያም አምልጠው ወደ አራራት ሸሹ። ልጁ አስራዶንም በምትኩ ነገሠ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.