Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ነገሥት 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ሆሴዕ የመጨረሻው የእስራኤል ንጉሥ
1፥3-7 ተጓ ምብ – 2ነገ 1፥9-12

1 የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዘጠኝ ዓመትም ገዛ።

2 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ክፉ ሥራው ግን ከርሱ አስቀድሞ የነበሩት የእስራኤል ነገሥታት የፈጸሙትን ያህል አልነበረም።

3 የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ሊወጋው መጣ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፤ ገበረለትም።

4 የአሦር ንጉሥ ግን ሆሴዕ እንደ ከዳው ተገነዘበ፤ ምክንያቱም ወደ ግብጽ ንጉሥ ወደ ሲጎር መልክተኞች ስለ ላከና በየዓመቱም ያደርግ እንደ ነበረው ለአሦር ንጉሥ ስላልገበረ ነው፤ ከዚህም የተነሣ ስልምናሶር ይዞ ወህኒ ቤት አስገባው።

5 የአሦርም ንጉሥ አገሩን በሙሉ ወረረ፤ ወደ ሰማርያም ገሥግሦ ሦስት ዓመት ከበባት።

6 በሆሴዕ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም በምርኮ ወደ አሦር አፈለሳቸው። እነዚህም በአላሔ፣ ጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብ እንዲሁም በማዴ ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ።


እስራኤላውያን በኀጢአታቸው ምክንያት ተማረኩ

7 እንግዲህ እስራኤላውያን ይህ ሁሉ ሊደርስባቸው የቻለው፣ ከግብጽ ምድር ከፈርዖን አገዛዝ ከግብጽ ንጉሥ ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ስለ በደሉት ነው፤ እንዲሁም ሌሎች አማልክትን በማምለክ፣

8 እግዚአብሔር ከፊታቸው አሳድዶ ያወጣቸውን የአሕዛብንና የእስራኤልም ነገሥታት ወደ ምድሪቱ ያገቡትን አስጸያፊ ልማድ ስለ ተከተሉ ነበር።

9 እስራኤላውያን በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ትክክል ያልሆነ ነገር በስውር አደረጉ፤ ከቃፊር መጠባበቂያ ማማ አንሥቶ እስከ ተመሸገው ከተማ ባሉት መኖሪያዎቻቸው ሁሉ በሚገኙት ኰረብቶች ላይ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ።

10 በእያንዳንዱ ኰረብታ ላይና በእያንዳንዱም የተንሰራፋ ዛፍ ሥር ዐምደ ጣዖትና የአሼራን ምስል ዐምዶች አቆሙ።

11 እግዚአብሔር ከፊታቸው አሳድዶ ያስወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉትም ሁሉ፣ በየኰረብታው ላይ ዕጣን አጤሱ፤ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጣ ክፉ ነገር አደረጉ።

12 እግዚአብሔር፣ “ይህን ማድረግ አይገባችሁም” ቢላቸውም እንኳ እነርሱ ጣዖታትን አመለኩ።

13 ይህም ሆኖ እግዚአብሔር፣ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ አባቶቻችሁ እንዲፈጽሙት ባዘዝኋቸው ሕግ ሁሉ መሠረት እንዲሁም በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት ለእናንተ ባስተላለፍሁት ሕግ መሠረት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ጠብቁ” ብሎ በነቢያቱና በባለራእዮች ሁሉ እስራኤልንና ይሁዳን አስጠንቅቆ ነበር።

14 ይሁን እንጂ እነዚህም አልሰሙም፤ እግዚአብሔር አምላካቸውን እንዳልታመኑበት እንደ አባቶቻቸው ዐንገታቸውን አደነደኑ።

15 ሥርዐቱንና ከአባቶቻቸው ጋራ የገባውን ኪዳን፣ ለእነርሱም የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ናቁ፤ ከንቱ ጣዖታትን ተከትለው ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ፤ እግዚአብሔር፣ “እነርሱ የሚያደርጉትን እንዳታደርጉ” ብሎ ቢያዝዛቸው እንኳ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ፤ እግዚአብሔር እንዳያደርጉ የከለከላቸውንም ፈጸሙ እንጂ አልተዉም።

16 አምላካቸው እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሁሉ አልፈጸሙም፤ አቅልጠውም ሁለት የጥጃ ምስልና የአሼራን ምስል ዐምድ ሠሩ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰገዱ፤ በኣልን አመለኩ፤

17 እንዲሁም ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። ጥንቈላና መተት አደረጉ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ፤ ለቍጣም አነሣሡት።

18 ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ የይሁዳ ነገድ ብቻ ሲቀር እስራኤልን ከፊቱ አራቀ።

19 ይሁዳም ቢሆን ከእስራኤል የተቀበለውን ልማድ ተከተለ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም።

20 ስለዚህ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ ተዋቸው፤ አስጨነቃቸው፤ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸውም ድረስ በማራኪዎቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።

21 እስራኤልን ከዳዊት ቤት ከለየ በኋላ፣ እነርሱ የናባጥን ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እስራኤል እግዚአብሔርን እንዳይከተል በማሳት ትልቅ ኀጢአት እንዲሠራ አደረገ።

22 እስራኤላውያንም በኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ ጸኑ፤ ከዚያም አልተመለሱም።

23 እግዚአብሔር በባሪያዎቹ በነቢያት ሁሉ አማካይነት ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸው ድረስ በዚያው ቀጠሉበት፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ከሀገሩ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደ፤ አሁንም በዚያው ይገኛል።


አሦራውያን በሰማርያ ሰፈሩ

24 የአሦርም ንጉሥ ሕዝቡን ከባቢሎን፣ ከኩታ፣ ከአዋና ከሐማት፣ ከሴፈርዋይም ከተሞች አምጥቶ በእስራኤላውያን ቦታ እንዲገቡ በሰማርያ ከተሞች አሰፈራቸው፤ እነርሱም ሰማርያን ወርሰው በከተሞቿ ይኖሩ ጀመር።

25 በዚያ መኖር እንደ ጀመሩም እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አንበሶች ሰደደባቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹን ሰብረው ገደሉ።

26 ለአሦርም ንጉሥ፣ “ወደ ሰማርያ ከተሞች ወስደህ ያሰፈርኸው ሕዝብ የዚያ አገር አምላክ የሚፈልገውን አላወቀም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰብሮ የሚገድል አንበሳ ላከበት” የሚል ወሬ ደረሰው።

27 ከዚያም የአሦር ንጉሥ፣ “ከሰማርያ ማርካችሁ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን፣ በዚያው እንዲኖር መልሳችሁ ውሰዱትና የአገሩ አምላክ ምን እንደሚፈልግ ሕዝቡን ያስተምር” ሲል አዘዘ።

28 ስለዚህ ከሰማርያ ማርከው ከወሰዷቸው ካህናት አንዱ ወደ ቤቴል ተመልሶ እግዚአብሔርን እንዴት መፍራት እንደሚገባቸው አስተማራቸው።

29 ያም ሆኖ ግን እያንዳንዱ ወገን በየሰፈረበት ከተማ የራሱን አምላክ ሠራ፤ ያንም ቀድሞ የሰማርያ ሕዝብ በኰረብታው ላይ በሠራው ማምለኪያ እየወሰደ አቆመ።

30 ከባቢሎን የመጡት ሱኮት በኖትን፣ ከኩታ የመጡት ኔርጋልን፣ ከሐማት የመጡት አሲማትን ሠሩ፤

31 አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅ የተባሉትን አማልክት ሲሠሩ፣ ከሴፈርዋይም የመጡት ደግሞ አድራሜሌክና አናሜሌክ ለተባሉት አማልክታቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ።

32 እግዚአብሔርን አመለኩ፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ወገን የመጣበትን ሕዝብ ልማድ ተከትሎ፣ በየኰረብታው ባሉት ቤተ ጣዖታት የሚያገለግሉትን ካህናት ሾመ።

33 በአንድ በኩል እግዚአብሔርን ሲያመልኩ፣ በሌላ በኩል ግን እንደየአገራቸው ልማድ የየራሳቸውን አማልክት ያመልኩ ነበር።

34 ይህንም ልማዳቸውን እስከ ዛሬ ድረስ አልተዉትም፤ እግዚአብሔርን በአግባቡ አያመልኩም፤ እንዲሁም እስራኤል ብሎ ለጠራው ለያዕቆብ ዘሮች የሰጣቸውን ሥርዐቶችና ደንቦች፣ ሕጎችና ትእዛዞችን አይከተሉም።

35 እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋራ ኪዳን ሲገባ እንዲህ ሲል አዝዟቸው ነበር፤ “ሌሎችን አማልክት አትፍሯቸው፤ አትስገዱላቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትሠዉላቸውም፤

36 መፍራት የሚገባችሁ ግን በታላቅ ኀይልና በተዘረጋች ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን ብቻ ነው። ለርሱ ስገዱ፤ ለርሱም መሥዋዕት አቅርቡ።

37 የጻፈላችሁን ሥርዐቶችና ደንቦች፣ ሕጎችና ትእዛዞች ምን ጊዜም ተግታችሁ ጠብቁ። ሌሎች አማልክትን አታምልኩ።

38 ከእናንተ ጋራ የገባሁትን ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎች አማልክትም አታምልኩ።

39 ይልቅስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ የሚታደጋችሁ እርሱ ነውና።”

40 ነገር ግን በቀደመው ልማዳቸው ጸኑ እንጂ አልተመለሱም።

41 እነዚህ ሕዝቦች ምንም እንኳ በአንድ ወገን እግዚአብሔርን ቢያመልኩትም፣ የተቀረጹ ምስሎቻቸውንም ያገለግሉ ነበር። ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው ያደረጉትን ዛሬም እንደ ቀጠሉበት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告