Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ነገሥት 15 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ
1፥1-7 ተጓ ምብ – 2ዜና 26፥3-4 ፤ 26፥21-23

1 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያ ሰባተኛው፣ ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ ነገሠ።

2 በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ዐምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።

3 እርሱም አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።

4 ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።

5 እግዚአብሔርም ንጉሡን ቀሠፈው፤ እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጽ ነበረበት፤ በተለየ ቤትም ይኖር ነበር። በዚያ ጊዜ ቤተ መንግሥቱን በኀላፊነት የሚመራውና የአገሩንም ሕዝብ የሚያስተዳድረው የንጉሡ ልጅ ኢዮአታም ነበር።

6 በዓዛርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

7 ዓዛርያስ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ በአባቶቹ መቃብር አጠገብ ቀበሩት። ልጁ ኢዮአታምም በምትኩ ነገሠ።


የእስራኤል ንጉሥ ዘካርያስ

8 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት፣ የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ስድስት ወርም ገዛ።

9 አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

10 የኢያቤስ ልጅ ሰሎም በዘካርያስ ላይ አሤረበት፤ በሕዝቡ ፊት አደጋ ጥሎ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ።

11 በዘካርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቧል።

12 በዚህም እግዚአብሔር ለኢዩ፣ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ” ሲል የተናገረው ቃል ተፈጸመ።


የእስራኤል ንጉሥ ሰሎም

13 የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም በእስራኤል ላይ ነገሠ። በሰማርያ ተቀምጦ አንድ ወር ገዛ።

14 የጋዲ ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ በመሄድ አደጋ ጥሎ የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን ገደለው፤ ከዚያም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

15 በሰሎም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራና የጠነሰሰውም ሤራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፏል።

16 በዚያ ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ በቲፍሳና በከተማዪቱ ነዋሪዎች ላይ ሁሉ፣ በአካባቢዋም ጭምር አደጋ ጣለ፤ ይህን ያደረገውም የከተማዪቱን በሮች ለመክፈት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ነበር፤ ቲፍሳን መታት፤ የነፍሰጡሮችንም ሆድ ሁሉ ቀደደ።


የእስራኤል ንጉሥ ምናሔም

17 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት፣ የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያ ተቀምጦም ዐሥር ዓመት ገዛ።

18 በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ በዘመኑም ሁሉ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

19 ከዚያም የአሦር ንጉሥ ፎሓ ምድሪቱን ወረረ፤ ምናሔም ርዳታውን ለማግኘትና በመንግሥቱ ላይ ያለውን ይዞታ ለማጽናት ሲል፣ አንድ ሺሕ መክሊት ብር ሰጠው።

20 ምናሔም ገንዘቡ እንዲዋጣ ያደረገው ከእስራኤል ሲሆን፣ ይህንም ያደረገው ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ እያንዳንዱ ሀብታም ዐምሳ፣ ዐምሳ ሰቅል ብር እንዲያዋጣ በማስገደድ ነበር። ስለዚህ የአሦር ንጉሥ በዚያች አገር አልቈየም፤ ተመልሶ ሄደ።

21 በምናሔም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

22 ምናሔም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ፋቂስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።


የእስራኤል ንጉሥ ፋቂስያስ

23 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በዐምሳኛው ዓመት፣ የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በሰማርያ ከተማ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ።

24 ፋቂስያስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም፣ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

25 ከጦር አለቆቹ አንዱ የሆነው የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ አሤረበት፤ ዐምሳ የገለዓድ ሰዎች ይዞ በመሄድ፣ ሰማርያ ቤተ መንግሥት ባለው ምሽግ ፋቂስያስን ከአርጎብና ከአርያ ጋራ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ።

26 በፋቂስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፏል።


የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ

27 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በዐምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በሰማርያ ከተማ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሃያ ዓመትም ገዛ።

28 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

29 በእስራኤል ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን፣ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮን፣ አቤልቤትመዓካን፣ ያኖዋን፣ ቃዴስንና አሦርን፣ ገለዓድንና ገሊላን፣ የንፍታሌምንም ምድር ጭምር ያዘ፤ ሕዝቡንም ማርኮ ወደ አሦር ወሰደው።

30 ከዚያም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ አሤረበት፤ አደጋ ጥሎም ገደለው፤ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም በነገሠ በሃያኛው ዓመትም ሆሴዕ በፋቁሔ እግር ተተክቶ ነገሠ።

31 በፋቁሔ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸማቸውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?


የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአታም
15፥33-38 ተጓ ምብ – 2ዜና 2፥1-4 ፤ 2፥7-9

32 የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ።

33 በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ ኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ስትሆን፣ ኢየሩሳ ትባል ነበር።

34 አባቱ ዖዝያን እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።

35 ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር። ኢዮአታም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የላይኛውን በር ሠራ።

36 በኢዮአታም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

37 በዚያ ጊዜ እግዚአብሔር የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔን ይሁዳን እንዲወጉ አደረገ።

38 ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ አባቶቹ በተቀበሩበትም በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝም በምትኩ ነገሠ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告