2 ነገሥት 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምጎቶልያና ኢዮአስ 11፥1-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 22፥10–23፥21 1 የአካዝያስ እናት ጎቶልያ ልጇ መሞቱን ባየች ጊዜ፣ ንጉሣውያን ቤተ ሰብ በሙሉ አጠፋች። 2 የንጉሥ ኢዮራም ልጅ፣ የአካዝያስ እኅት ዮሳቤት ግን የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሊገደሉ ከነበሩት ልዑላን መካከል ሰርቃ ወሰደችው። እንዳይገደልም ከጎቶልያ በመደበቅ እርሱንና ሞግዚቱን በአንድ እልፍኝ ሸሸገቻቸው። 3 እርሱም ጎቶልያ ምድሪቱን በምትገዛበት ጊዜ ከሞግዚቱ ጋራ በእግዚአብሔር ቤት ተደብቆ ስድስት ዓመት ኖረ። 4 በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ ካራውያንንና ዘብ ጠባቂዎቹን የሚያዝዙትን የመቶ አለቆች እርሱ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲመጡ አደረገ። ከእነርሱም ጋራ ቃል ኪዳን በማድረግ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አስማላቸው፤ ከዚያም የንጉሡን ልጅ አሳያቸው። 5 እንዲህም ሲል አዘዛቸው፤ “እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሦስት ምድብ ሆናችሁ በሰንበት ዕለት ዘብ ከምትጠብቁት መካከል አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤ 6 ሌላው ከሦስት እጅ አንዱ የሱርን በር ይጠብቅ፤ የቀረው ሌላው አንድ ሦስተኛው እጅ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ተራ ገብቶ ከሚጠብቀው ከዘብ ጥበቃው ኋላ ያለውን በር ይጠብቅ። 7 እናንተ እንደተለመደው በሰንበት ዕለት ከዘብ ጥበቃ ነጻ የምትሆኑት ሁለት ሦስተኛው እጅ ግን ንጉሡ ያለበትን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ጠብቁ። 8 እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ ይዞ በንጉሡ ዙሪያ ሁኑ፤ የሚቀርባችሁ ማንም ሰው ቢኖር ግን ይገደል። ንጉሡ በሚወጣበትም ሆነ በሚገባበት ጊዜ ሁሉ ዐብራችሁት ሁኑ።” 9 የመቶ አለቆቹም ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዘው አደረጉ፤ እያንዳንዳቸውም በሰንበት ዕለት ለዘብ ጥበቃ የሚገቡትንና ከዘብ ጥበቃ የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ። 10 ካህኑም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊትን ጦሮችና ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው። 11 ወታደሮቹም እያንዳንዱ መሣሪያውን በእጁ ይዞ፣ ከቤተ መቅደሱ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ ቆሙ። 12 ዮዳሄም የንጉሡን ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነለት፤ ኪዳኑንም ሰጠው፤ መንገሡን ዐወጁ፤ ቀብተውም አነገሡት። ከዚያም ሕዝቡ፣ “ንጉሡ ሺሕ ዓመት ይንገሥ” እያሉ በማጨብጨብ ደስታቸውን ከፍ ባለ ድምፅ ገለጹ። 13 ጎቶልያም የሰራዊቱንና የሕዝቡን ጩኸት ስትሰማ፣ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደች። 14 እነሆ፤ በወጉ መሠረት ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ፣ ሹማምቱና መለከት ነፊዎቹ ከአጠገቡ ሆነው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይፈነጥዝ፣ መለከትም ይነፋ ነበር። ጎቶልያም ልብሷን ቀድዳ፣ “ይህ ክሕደት ነው! ክሕደት ነው!” ብላ ጮኸች። 15 ካህኑ ዮዳሄም የወታደሮች አዛዥ ወደሆኑት የመቶ አለቆች፣ “በረድፍ በተሰለፉት ጭፍሮች መካከል አውጧት፤ የሚከተላትንም ሁሉ በሰይፍ ግደሉት” ሲል አዘዘ፤ ይህ የሆነውም ካህኑ አስቀድሞ፣ “በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገደል የለባትም” በማለቱ ነበር። 16 ስለዚህ ፈረሶች ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚገቡበት መንገድ ስትደርስ ያዟት፤ በዚያም ተገደለች። 17 ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን እንዲመሠረት አደረገ፤ እንደዚሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን መሠረተ። 18 ከዚያም የአገሩ ሕዝብ ሁሉ ሄደው የበኣልን ቤተ ጣዖት አፈራረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሰባበሩ፤ የበኣልን ካህን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት። ካህኑ ዮዳሄም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚጠብቁ ዘበኞችን መደበ። 19 ከዚያም መቶ አለቆቹን፣ ካራውያንንና ዘበኞቹን እንዲሁም የአገሩን ሕዝብ በሙሉ በመያዝ ሁሉም በአንድነት ሆነው፣ ንጉሡን ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወስደው በዘብ ጠባቂዎች ቅጥር በር በኩል ታች ወዳለው ቤተ መንግሥት ይዘውት ገቡ፤ ንጉሡም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ 20 የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ተደሰተ፤ ጎቶልያ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሰይፍ ተገድላ ስለ ነበር፣ ከተማዪቱ ጸጥ አለች። 21 ኢዮአስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.