2 ቆሮንቶስ 7 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 እንግዲህ፣ ወዳጆች ሆይ፤ ይህ የተስፋ ቃል ስላለን፣ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርገው። የጳውሎስ ደስታ 2 ልባችሁን አስፉልን፤ እኛ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም ወደ ብልሹነት አልመራንም፤ ማንንም አላታለልንም። 3 ይህን የምለው ልኰንናችሁ አይደለም፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደ ነገርኋችሁ፣ በልባችን ውስጥ ስፍራ አላችሁ፤ ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም ዐብረን ነው። 4 በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ትልቅ ነው፤ በእናንተም ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ እንዲሁም እጅግ ተጽናንቻለሁ፤ በመከራችንም ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም። 5 ወደ መቄዶንያ በመጣን ጊዜ፣ ከየአቅጣጫው መከራ ደረሰብን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አላገኘም፤ ከውጭ ጠብ፣ ከውስጥ ደግሞ ፍርሀት ነበረብን። 6 ይሁን እንጂ ሐዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን። 7 የተጽናናነውም በመምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱንም ልታጽናኑት በመቻላችሁ ጭምር ነው። ስለ ናፍቆታችሁ፣ ስለ ሐዘናችሁና ለእኔም ስላላችሁ ቅናት ነግሮናል፤ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ ብሎኛል። 8 በመልእክቴ ባሳዝናችሁም በዚህ አልጸጸትም፤ ብጸጸትም እንኳ መልእክቴ ያሳዘናችሁ ለጥቂት ጊዜ እንደ ሆነ ተረድቻለሁ። 9 አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ ደስታዬም ስላዘናችሁ ሳይሆን፣ ሐዘናችሁ ንስሓ ለመግባት ስላበቃችሁ ነው፤ ምክንያቱም ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ ከእኛ የተነሣ ምንም አልተጐዳችሁም። 10 እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሐዘን ወደ ድነት ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም። ዓለማዊ ሐዘን ግን ለሞት ያበቃል። 11 ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነው ሐዘን እንዴት ያለ ትጋት፣ እንዴት ያለ መልስ የመስጠት ችሎታ፣ እንዴት ያለ ቍጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሀት፣ እንዴት ያለ ናፍቆት፣ እንዴት ያለ በጎ ቅናት፣ እንዴት ያለ በቀል እንዳስገኘላችሁ ተመልከቱ። በዚህም ጕዳይ ንጹሓን መሆናችሁን በሁሉ ረገድ አስመስክራችኋል። 12 እንግዲህ እኔ የጻፍሁላችሁ ስለ በደለው ወይም ስለ ተበደለው ሰው አይደለም፤ ነገር ግን ለእኛ ምን ያህል ታማኞች እንደ ሆናችሁ፣ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን እንድታዩ በማለት ነው። 13 እኛም የተጽናናነው በዚህ ምክንያት ነው። ከእኛም መጽናናት በተጨማሪ በቲቶ ደስታ እኛም ይበልጥ ደስ ብሎናል፤ ምክንያቱም ሁላችሁም መንፈሱን አሳርፋችኋል። 14 በእናንተ ላይ ያለኝን ትምክሕት ለርሱ ነግሬው ነበር፤ እናንተም አላሳፈራችሁኝም። ነገር ግን ስንነግራችሁ የነበረው ሁሉ እውነት እንደ ሆነ፣ እንደዚሁም ስለ እናንተ ለቲቶ በትምክሕት የነገርነው እውነት መሆኑ ተረጋግጧል። 15 እርሱም በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደ ተቀበላችሁትና ሁላችሁም እንደ ታዘዛችሁ ሲያስታውስ ለእናንተ ያለው ፍቅር እየበረታ ሄዷል። 16 እኔም በማናቸውም ነገር ልተማመንባችሁ በመቻሌ ደስ ብሎኛል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.