2 ቆሮንቶስ 6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ከእግዚአብሔር ጋራ ዐብረን የምንሠራ እንደ መሆናችን መጠን፣ የተቀበላችሁትን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከንቱ እንዳታደርጉት ዐደራ እንላችኋለን። 2 እርሱ፣ “በተወደደ ጊዜ ሰማሁህ፤ በድነት ቀን ረዳሁህ” ይላልና። እነሆ፤ የተወደደው ጊዜ አሁን ነው፤ የመዳንም ቀን አሁን ነው። ጳውሎስ የተቀበለው መከራ 3 አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ ለማንም ዕንቅፋት መሆን አንፈልግም። 4 ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን፦ በብዙ ትዕግሥት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ 5 በመገረፍ፣ በመታሰር፣ በሁከት፣ በሥራ ብዛት፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመራብ፣ 6 በንጽሕና፣ በዕውቀት፣ በትዕግሥት፣ በቸርነት፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ በእውነተኛ ፍቅር፣ 7 በእውነት ቃል፣ በእግዚአብሔር ኀይል፣ በቀኝና በግራ እጅ የጽድቅ የጦር ዕቃ በመያዝ፣ 8 በክብርና በውርደት፣ በመመስገንና በመሰደብ ኖረናል፤ ደግሞም እውነተኞች ስንሆን ሐሰተኞች ተብለናል፤ 9 የታወቅን ስንሆን እንዳልታወቅን ሆነናል፤ ሞተዋል ስንባል እነሆ በሕይወት አለን፤ ብንደበደብም አልተገደልንም፤ 10 ሐዘንተኞች ስንሆን ሁልጊዜ ደስተኞች ነን፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 11 የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፤ ሁሉን በግልጽ ነግረናችኋል፤ ልባችንንም ወለል አድርገን ከፍተንላችኋል። 12 በእኛ አልተገደባችሁም፤ ነገር ግን በውስጣችሁ ተገድባችኋል። 13 ልጆቼ እንደ መሆናችሁ መጠን ይህን አሳስባችኋለሁ፤ እናንተም በዚያው ልክ ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱልን። ከማያምኑ ሰዎች ጋራ አለመተባበር 14 ከማያምኑ ሰዎች ጋራ አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዐመፅ ጋራ ምን ግንኙነት አለው? ብርሃንስ ከጨለማ ጋራ ምን ኅብረት አለው? 15 ክርስቶስ ከቤልሆር ጋራ ምን ስምምነት አለው? የሚያምን ከማያምን ጋራ ምን ኅብረት አለው? 16 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖታት ጋራ ምን ስምምነት አለው? እኛ እኮ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ “ከእነርሱ ጋራ እኖራለሁ፤ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፤ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” 17 “ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡ፤ ተለዩም፤ ይላል ጌታ። ርኩስ የሆነውን ነገር አትንኩ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ።” 18 “እኔ አባት እሆናችኋለሁ፤ እናንተም፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቼ ትሆናላችሁ፤ ይላል ሁሉን የሚችል ጌታ።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.