Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ቆሮንቶስ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 እንግዲህ ላሳዝናችሁ ስላልፈለግሁ ወደ እናንተ ዳግመኛ ላለመምጣት ወሰንሁ፤

2 እኔ ባሳዝናችሁም እንኳ፣ ከእናንተው ካሳዘንኋችሁ በቀር ደስ የሚያሠኘኝ ማን አለ?

3 ባለፈው ጊዜ እንደዚያ የጻፍሁላችሁ ወደ እናንተ ስመጣ ደስ ሊያሠኙኝ የሚገባቸው ሰዎች እንዳያሳዝኑኝ በማለት ነው፤ ምክንያቱም የእኔ ደስታ የሁላችሁ ደስታ እንደሚሆን አምናለሁ።

4 እንደዚያ ስጽፍላችሁ በትልቅ ሐዘንና በልብ ጭንቀት፣ በብዙም እንባ ውስጥ ነበርሁ፤ ይህንም ያደረግሁት ለእናንተ ያለኝን ጽኑ ፍቅር እንድታውቁ በማለት እንጂ እናንተን ለማሳዘን አልነበረም።


በደለኛን ይቅር ማለት

5 ማንም ሰውን ቢያሳዝን፣ ነገር ማግነን አይሁንብኝና፣ ያሳዘነው እኔን ብቻ ሳይሆን በመጠኑም ቢሆን ሁላችሁንም ነው።

6 እንደዚህ ያለው ሰው ብዙዎች የወሰኑበት ቅጣት በቂው ነው።

7 ደግሞም ከልክ በላይ ዐዝኖ ተስፋ እንዳይቈርጥ፣ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባችኋል።

8 ስለዚህ አሁንም የምትወድዱት መሆናችሁን እንድትገልጹለት እለምናችኋለሁ።

9 የጻፍሁላችሁም፣ የሚያጋጥማችሁን ፈተና መቋቋማችሁንና በሁሉም ነገር ታዛዦች መሆናችሁን ለማወቅ ነበር።

10 እናንተ ይቅር የምትሉትን ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ በርግጥ ይቅር የምለው ነገር ካለ፣ በክርስቶስ ፊት ይቅር የምለው ስለ እናንተ ስል ነው።

11 ይህንም የምናደርገው ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ ነው፤ የርሱን ዕቅድ አንስተውምና።


የአዲስ ኪዳን አገልጋዮች

12 የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በሄድሁ ጊዜ፣ ጌታ በር ከፍቶልኝ ነበር፤

13 ይሁን እንጂ ወንድሜን ቲቶን እዚያ ስላላገኘሁት መንፈሴ አላረፈም፤ ስለዚህ ተሰናብቻቸው ወደ መቄዶንያ ሄድሁ።

14 ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ በድል አድራጊነት እያዞረ ለሚመራን፣ የዕውቀቱንም መዐዛ በእኛ አማካይነት በየስፍራው ለሚገልጥ አምላክ ምስጋና ይሁን፤

15 ምክንያቱም በሚድኑትና በሚጠፉት መካከል ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዐዛ ነን።

16 ለሚጠፉት ወደ ሞት የሚወስድ የሞት ሽታ፣ ለሚድኑት ግን ወደ ሕይወት የሚወስድ የሕይወት ሽታ ነን፤ ታዲያ፣ ለዚህ ብቁ የሚሆን ማን ነው?

17 እኛ እኮ ትርፍ ለማግኘት ብለን የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላኩ ሰዎች በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት በቅንነት እንናገራለን።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告