Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ቆሮንቶስ 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ጳውሎስና ሐሰተኞች ሐዋርያት

1 ጥቂቱን ሞኝነቴን እንደምትታገሡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በርግጥም እየታገሣችሁኝ ነው።

2 በእግዚአብሔር ቅናት እቀናላችኋለሁ፤ እናንተን እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ባል ዐጭቻችኋለሁና።

3 ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰል እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ልቡና ተበላሽቶ ለክርስቶስ ካላችሁ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትወሰዱ እሠጋለሁ።

4 ምክንያቱም አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እኛ ከሰበክንላችሁ ኢየሱስ ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ፣ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ መንፈስ ብትቀበሉ፣ ወይም ከተቀበላችሁት ወንጌል የተለየ ወንጌል ብትቀበሉ፣ ነገሩን በዝምታ ታልፉታላችሁ ማለት ነው።

5 እኔ ግን “ታላላቅ ሐዋርያት” ከሚባሉት በምንም የማንስ አይመስለኝም።

6 የንግግር ችሎታ ባይኖረኝም እንኳ፣ ዕውቀት ግን አለኝ፤ ይህንም በሁሉ መንገድ በሚገባ ግልጽ አድርገንላችኋል።

7 እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ ለእናንተ መስበኬ እንደ ኀጢአት ተቈጥሮብኝ ይሆን?

8 እናንተን ለማገልገል ስል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ርዳታ በመቀበሌ እነርሱን ዘርፌአቸዋለሁ።

9 ከእናንተም ጋራ ሳለሁ አንዳች ባስፈለገኝ ጊዜ፣ ከመቄዶንያ የመጡ ወንድሞች የሚያስፈልገኝን ስለ ሰጡኝ ለማንም ሸክም አልሆንሁም። በእናንተ ላይ በምንም ነገር ሸክም እንዳልሆን ተጠንቅቄአለሁ፤ ወደ ፊትም እጠነቀቃለሁ።

10 የክርስቶስ እውነት በውስጤ እስካለ ድረስ፣ በአካይያ አውራጃ ይህን ትምክሕቴን ማንም ሊገታው አይችልም።

11 ይህን የምለው ለምንድን ነው? ስለማልወድዳችሁ ነውን? እንደምወድዳችሁ እግዚአብሔር ያውቃል።

12 ከእኛ ጋራ እኩል ለመሆን በሥራቸው እየተመኩ ቀን የሚጠብቁትን ሰዎች ምክንያት ለማሳጣት አሁን የማደርገውን ወደ ፊትም አደርጋለሁ።

13 እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለዋውጡ፣ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች ናቸው።

14 ይህም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም፤ ምክንያቱም ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል።

15 እንግዲህ የርሱ አገልጋዮች፣ የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለውጡ የሚያስገርም አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።


ጳውሎስ በደረሰበት መከራ ይመካል

16 እንደ ገና ይህን እላለሁ፤ ማንም ሰው እንደ ሞኝ አይቍጠረኝ፤ እናንተም የምትቈጥሩኝ ከሆነ፣ እኔም በጥቂቱ እንድመካ እንደ ሞኝ ተቀበሉኝ።

17 እንደዚህ ልበ ሙሉ ሆኜ የምናገረው እንደ ሞኝ እንጂ እንደ ጌታ ፈቃድ አይደለም።

18 ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔም ደግሞ እመካለሁ።

19 እናንተም ብልኆች ስለ ሆናችሁ ሞኞችን በደስታ ትታገሣላችሁ፤

20 ማንም ተነሥቶ ባሪያ ቢያደርጋችሁ፣ ቢበዘብዛችሁ፣ ለጥቅሙ ሲል ቢጠጋችሁ፣ ቢንቀባረርባችሁ ወይም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁ።

21 እኛ ግን ለዚያ እጅግ ደካሞች መሆናችንን እያፈርሁ እናገራለሁ። ማንም በድፍረት በሚመካበት ነገር ሁሉ እኔም ደፍሬ መመካት እንደምችል እንደ ሞኝ እናገራለሁ።

22 እነርሱ ዕብራውያን ናቸውን? እኔም ነኝ፤ እስራኤላውያን ናቸውን? እኔም ነኝ፤ የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔም ነኝ።

23 የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? አእምሮውን እንደ ጣለ ሰው ልናገርና እኔ እበልጣቸዋለሁ፤ ደግሞም ብዙ ጊዜ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ታስሬአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገርፌአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ለሞት ተቃርቤአለሁ።

24 አይሁድ ለአርባ ጅራፍ አንድ የቀረው ዐምስት ጊዜ ገርፈውኛል።

25 ሦስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤአለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬአለሁ፤ ሦስት ጊዜ የመርከብ አደጋ ደርሶብኛል፤ አንድ ሌሊትና ቀን በባሕር ላይ ዐድሬአለሁ፤

26 ብዙ ጊዜ በጕዞ ተንከራትቻለሁ፤ ደግሞም ለወንዝ ሙላት አደጋ፣ ለወንበዴዎች አደጋ፣ ለገዛ ወገኖቼ አደጋ፣ ለአሕዛብ አደጋ፣ ለከተማ አደጋ፣ ለገጠር አደጋ፣ ለባሕር አደጋ እንዲሁም ለሐሰተኞች ወንድሞች አደጋ ተጋልጬ ነበር።

27 ብዙ ጥሬአለሁ፤ ብዙ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ አጥቻለሁ፤ ተርቤአለሁ፤ ተጠምቻለሁ፤ ብዙ ጊዜ ምግብ ሳልቀምስ ኖሬአለሁ፤ በብርድና በዕራቍትነት ተቈራምጃለሁ።

28 ሌላውን ነገር ሳልቈጥር፣ ዕለት ዕለት የሚያስጨንቀኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሐሳብ ነው።

29 ደካማ ማን ነው? እኔስ አብሬ አልደክምምን? በኀጢአት የሚሰናከል ማን ነው? እኔስ አልቈጭምን?

30 መመካት ካለብኝ፣ ደካማነቴን በሚያሳዩ ነገሮች እመካለሁ።

31 ለዘላለም የተመሰገነው የጌታ የኢየሱስ አምላክና አባት እንደማልዋሽ ያውቃል።

32 ደማስቆ ሳለሁ ከንጉሥ አርስጦስዮስ በታች የሆነው ገዥ ሊያስይዘኝ ፈልጎ፣ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር።

33 ነገር ግን በግንቡ መስኮት በኩል በቅርጫት አውርደውኝ ከእጁ አመለጥሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告