2 ዜና መዋዕል 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየሳባ ንግሥት ሰሎሞንን ጐበኘች 9፥1-12 ተጓ ምብ – 1ነገ 10፥1-13 1 የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። ቅመማ ቅመም፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮችን በግመሎች አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋራ ደረሰች፤ ወደ ሰሎሞንም ቀርባ በልቧ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። 2 ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ከሰሎሞን የተሰወረና ሊመልስላት ያልቻለው አንድም ጥያቄ አልነበረም 3 የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ፣ የሠራውን ቤተ መንግሥት፣ 4 እንዲሁም በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ የአስተናባሪዎቹን አቋቋምና የደንብ ልብሳቸውን፣ ጠጅ አሳላፊዎቹንና አለባበሳቸውን እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ባየች ጊዜ እጅግ ተደነቀች። 5 ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስለ ተናገርሃቸው ነገሮችና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት እውነት ነው። 6 ይሁን እንጂ መጥቼ የነገሩኝን በዐይኔ እስካይ ድረስ አላመንሁም ነበር፤ በርግጥም የጥበብህ ታላቅነት እኩሌታው እንኳ አልተነገረኝም፤ እኔ ከሰማሁት ዝና እጅግ ይልቃል። 7 ሰዎችህ እንዴት ብፁዓን ናቸው! ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙ ሹማምትህስ ምንኛ ብፁዓን ናቸው! 8 በአንተ ደስ ተሰኝቶ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ንጉሥ ሆነህ እንድትገዛ፣ በዙፋኑ ላይ ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን፤ አምላክህ ለእስራኤል ካለው ፍቅርና ለዘላለም ሊያጸናቸው ካለው ፍላጎት የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን ታደርግ ዘንድ አንተን በላያቸው ላይ አንግሦሃል።” 9 ከዚያም ለንጉሡ አንድ መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ቅመማ ቅመሞችና የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰሎሞን እንደ ሰጠችው ዐይነት ቅመማ ቅመም ያለ ከቶ አልነበረም። 10 የኪራም ሰዎችና የሰሎሞን ሰዎች ከኦፊር ወርቅ እንደዚሁም ሰንደልና የከበሩ ድንጋዮች አመጡ። 11 ንጉሡም የሰንደሉን ዕንጨት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ ደረጃ መሥሪያ እንደዚሁም ለመዘምራኑ የመሰንቆና የበገና መሥሪያ አደረገው፤ ይህን የመሰለ ነገር በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም። 12 ንጉሥ ሰሎሞን ለሳባ ንግሥት የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ስጦታውም እርሷ ካመጣችለት በላይ ነበር። ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋራ ወደ አገሯ ተመለሰች። የሰሎሞን ብልጽግና 9፥13-28 ተጓ ምብ – 1ነገ 10፥14-29 ፤ 2ዜና 1፥14-17 13 ለሰሎሞን በየዓመቱ የሚገባለት ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት የሚመዝን ወርቅ ነበር። 14 ይህም ከታላላቅና ከተራ ነጋዴዎች ከሚገባው ቀረጥ ሌላ ነበር። መላው የዐረብ ነገሥታትና አገረ ገዦች ለሰሎሞን ወርቅና ብር ያመጡለት ነበር። 15 ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ከጥፍጥፍ ወርቅ ትላልቅ ጋሻዎችን አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ስድስት መቶ ሰቅል ጥፍጥፍ ወርቅ ነበር። 16 እንዲሁም ከጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎችን አበጀ፤ በእነዚህም በእያንዳንዱ ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን “የሊባኖስ ደን” በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖረ። 17 ከዚያም ንጉሡ በዝኆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን ሠርቶ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው። 18 ዙፋኑ ባለስድስት ደረጃ ሲሆን፣ ከዙፋኑ ጋራ የተያያዘ ከወርቅ የተሠራ የእግር መርገጫ ነበረው። መቀመጫውም ግራና ቀኙ መደገፊያ ያለው ሲሆን፣ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመዋል። 19 በስድስቱም ደረጃዎች ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለ ዙፋን በየትኛውም አገር መንግሥት ተሠርቶ አያውቅም። 20 ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ዋጋ እንደሌለው ስለሚቈጠር ከብር የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም። 21 ንጉሡ በኪራም ሰዎች የሚነዱ የተርሴስ መርከቦች ነበሩት፤ እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች እየያዙ ይመለሱ ነበር። 22 ንጉሥ ሰሎሞን በሀብትም ሆነ በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር። 23 የምድር ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ከሰሎሞን ጋራ መገናኘት ይፈልጉ ነበር። 24 በየዓመቱም የሚመጣው ሰው ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ ልብስ፣ የጦር መሣሪያ፣ ቅመማ ቅመም፣ ፈረስና በቅሎ ስጦታ አድርጎ ያመጣለት ነበር። 25 ሰሎሞን አራት ሺሕ የፈረሶችና የሠረገሎች ጋጥ ነበረው፤ እንዲሁም ንጉሡ በሚኖርበት በኢየሩሳሌምና በሠረገላ ከተሞች ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት። 26 እርሱም ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብጽ ዳርቻ ድረስ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ላይ ገዛ። 27 ንጉሡ በኢየሩሳሌም ብሩን እንደ ማንኛውም ድንጋይ፣ የዝግባውንም ዕንጨት ብዛት በየኰረብታው ግርጌ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። 28 የሰሎሞን ፈረሶች የመጡት ከግብጽና ከሌሎች አገሮች ነበር። የሰሎሞን መሞት 9፥29-31 ተጓ ምብ – 1ነገ 11፥41-43 29 የቀረው፣ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከናወነው ሥራ፣ ጥበቡም በነቢዩ በናታን ታሪክና በሴሎናዊው በአኪያ ትንቢት እንዲሁም ባለራእዩ አዶ ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው ራእይ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 30 ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ተቀምጦ በመላው እስራኤል ላይ አርባ ዓመት ነገሠ። 31 ከዚያም ሰሎሞን ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማ ቀበሩት። ልጁም ሮብዓም በርሱ ፈንታ ነገሠ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.