Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ሰሎሞን ያከናወናቸው ሌሎች ሥራዎች
8፥1-18 ተጓ ምብ – 1ነገ 9፥10-28

1 ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የራሱን ቤተ መንግሥት ሠርቶ በፈጸመበት በሃያኛው ዓመት መጨረሻ፣

2 ኪራም ለሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች አድሶ እስራኤላውያን እንዲሰፍሩባቸው አደረገ።

3 ከዚያም ሰሎሞን ወደ ሐማት ሱባ ዘመተ፤ ያዛትም።

4 በምድረ በዳውም ውስጥ ተድሞርንና ቀድሞ በሐማት ሠርቷቸው የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ ሠራ።

5 እንዲሁም የላይኛውን ቤትሖሮንና የታችኛውን ቤትሖሮን የተመሸጉ ከተሞች አድርጎ ከቅጥሮቻቸው፣ ከበሮቻቸውና ከመዝጊያዎቻቸው ጋራ ሠራ።

6 ደግሞም ባዕላትንና የሰሎሞን ዕቃ ማከማቻ ከተሞች፣ እንዲሁም ሠረገለኞችና ፈረሰኞች የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ሁሉ፣ በአጠቃላይ በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በግዛቶቹ ሁሉ ለመሥራት የፈለጋቸውን ነገሮች ሁሉ ሠራ።

7 እስራኤላውያን ያልሆኑትን ከኬጢያውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን የተረፉትን ሕዝቦች ሁሉ፣

8 እስራኤላውያን ያላጠፏቸውን፣ በምድሪቱ የቀሩትን የእነዚህን ሕዝቦች ዘሮች እስከ ዛሬ ድረስ እንደሚደረገው የጕልበት ሥራ ይሠሩ ዘንድ ሰሎሞን መለመላቸው፤

9 ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ ይልቁንም እነርሱ ወታደሮቹ፣ ሹማምቱ፣ የጦር አዛዦቹ፣ ሻምበሎቹ፣ የፈረሰኞችና የሠረገለኞች አዛዦቹ ነበሩ።

10 ከእነዚህም ሁለት መቶ ዐምሳዎቹ የንጉሥ ሰሎሞን ሹማምት ሰዎቹን የሚቈጣጠሩ ነበሩ።

11 ሰሎሞንም፣ “የእግዚአብሔር ታቦት የገባበት ቦታ ሁሉ ቅዱስ ስለ ሆነ፣ ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤተ መንግሥት መኖር አይገባትም” በማለት የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ እርሱ ወደ ሠራላት ቤተ መንግሥት አመጣት።

12 ሰሎሞንም በቤተ መቅደሱ መመላለሻ ፊት ለፊት ባሠራው የእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ።

13 ሙሴ ስለ መሥዋዕት አቀራረብ ባዘዘው መሠረት በእያንዳንዱ የበዓል ቀን ይኸውም በየሰንበቱ፣ በየወሩ መባቻና በሦስቱ የዓመት በዓላት ማለትም በቂጣ በዓል፣ በሰባቱ ሱባዔ የመከር በዓልና በዳስ በዓል ጊዜ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ።

14 የአባቱን የዳዊትን ሥርዐት በመከተልም፣ ካህናቱን በየአገልግሎት ክፍላቸው ሌዋውያኑንም ምስጋናውን እንዲመሩና በየዕለቱ ሥራቸው ካህናቱን እንዲረዱ መደባቸው። ደግሞም የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ባዘዘው መሠረት፣ የቤተ መቅደሱን በር ጠባቂዎች በልዩ ልዩ በሮች ጥበቃ ላይ በየክፍላቸው መደባቸው።

15 እነርሱም ንጉሡ ግምጃ ቤቱን ጨምሮ ስለ ማንኛውም ነገር ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የሰጠውን ትእዛዝ አልተላለፉም ነበር።

16 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ከተጣለበት ዕለት አንሥቶ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለው የሰሎሞን ሥራ ሁሉ ተከናወነለት፤ በዚሁ ሁኔታም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ከፍጻሜ ደረሰ።

17 ከዚያም ሰሎሞን በኤዶም ምድር የባሕር ጠረፍ ወደሚገኙት ወደ ዔጽዮንጋብርና ወደ ኤላት ሄደ።

18 ኪራምም ባሕሩን በሚያውቁት በራሱ መኰንኖች የሚታዘዙ መርከቦችን ላከለት፤ እነዚህም ከሰሎሞን ሰዎች ጋራ በመሆን ወደ ኦፊር ተጓዙ፤ ከዚያም አራት መቶ ዐምሳ መክሊት ወርቅ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን አመጡ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告