2 ዜና መዋዕል 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሠራው ሥራ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ አባቱ ዳዊት የቀደሰውን ብሩንና ወርቁን፣ ዕቃዎቹንም ሁሉ አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አኖራቸው። ታቦቱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ 5፥2–6፥11 ተጓ ምብ – 1ነገ 8፥1-21 2 ከዚያም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን እንዲያመጡ፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የእስራኤልን ነገድ አለቆችና የእስራኤልን ጐሣዎች ሹማምት ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 3 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ የሰባተኛው ወር በዓል በሚከበርበት ጊዜ፣ በንጉሡ ፊት ተሰበሰቡ። 4 የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በመጡ ጊዜ ሌዋውያኑ ታቦቱን አነሡ፤ 5 ታቦቱን፣ የመገናኛውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አመጡ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ተሸከሟቸው። 6 ንጉሥ ሰሎሞንና ዐብሮት በዚያ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤ ስፍር ቍጥር የሌላቸውን በጎችና በሬዎች በታቦቱ ፊት ሠዉ። 7 ከዚያም ካህናቱ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አምጥተው የቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ አግብተው ከኪሩቤል ክንፍ በታች ባለው ስፍራው አኖሩት። 8 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ከታቦቱ በላይ ባለው ስፍራ ላይ ዘርግተው፣ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ጋረዱ። 9 መሎጊያዎቹ በጣም ከመርዘማቸው የተነሣ ጫፎቻቸው ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ካለው ከቅድስት ይታዩ ነበር፤ ከቅድስት ወዲያ ላለ ሰው ግን አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ። 10 እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በኋላ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋራ ኪዳን ባደረገ ጊዜ፣ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በውስጡ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላት በቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም። 11 ካህናቱም ከቤተ መቅደሱ ወጡ፤ እዚያ የነበሩት ካህናት በምድባቸው መሠረት ባይሆንም፣ ሁሉም ራሳቸውን ቀድሰው ነበር። 12 መዘምራን የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፣ አሳፍ፣ ኤማን፣ ሄማንና ኤዶታም፣ ወንዶች ልጆቻቸውና የሥጋ ዘመዶቻቸው ሁሉ ያማረ ቀጭን በፍታ ለብሰው፣ ከመሠዊያው በስተምሥራቅ በኩል ቆመው ጸናጽል ይጸነጽሉ፣ በገና ይደረድሩና መሰንቆ ይመቱ ነበር፤ እነርሱም መለከት በሚነፉ አንድ መቶ ሃያ ካህናት ታጅበው ነበር። 13 መለከት ነፊዎችና ዘማሪዎችም በአንድነት አንድ ድምፅ ሆነው ለእግዚአብሔር ውዳሴና ምስጋና አቀረቡ፤ በመለከት፣ በጸናጽልና በሌሎች መሣሪያዎች ታጅበውም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እግዚአብሔርን እያወደሱ፣ “እርሱ ቸር ነው፣ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” እያሉ ዘመሩ። ከዚያም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በደመና ተሞላ። 14 የእግዚአብሔር ክብር የአምላክን ቤተ መቅደስ ሞልቶት ስለ ነበር፣ ከደመናው የተነሣ ካህናቱ አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.